Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት በጥንቃቄና በፍጥነት እየወሰደ የሚገኘው ህግ የማስከበር እርምጃ በስኬት ታጅቦ ወሳኝ የድል ምዕራፍ ተቀዳጅቷል- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግሥት በጥንቃቄና በፍጥነት እየወሰደ የሚገኘው ህግ የማስከበር እርምጃ በስኬት ታጅቦ ወሳኝ የድል ምዕራፍ መቀዳጀቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መልእክት፥ “ውድ የሃገራችን ህዝቦች! እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን” ብለዋል።

“እነሆ ዛሬ! በሃገር መከላከያ ሰራዊታችን በሳል የውጊያ ጥበብ እና የትግል ወኔ የህውሃት ጁንታ ቡድን የከተመባትን የመቀሌ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል” ብለዋል።

መንግሥት በክልሉ በጥንቃቄ እና በፍጥነት እየወሰደ የሚገኘው ህግ የማስከበር እርምጃ በስኬት ታጅቦ ወሳኝ የድል ምዕራፍ መቀዳጀቱንም ገልፀዋል።

“ለዚህ ዘመን ተሻጋሪ ድል ላበቁን ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ ለአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና ሚሊሻዎች ታላቅ ምስጋና እና ክብር ይገባቸዋል” ብለዋል አቶ ደመቀ።

“በዚህ ህግ የማስከበር ዕርምጃ በኢትዮጵያዊነት ለአፍታ ለማይደራደረው የትግራይ ክልል ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊታችን ብርቱ ደጀን በመሆን ለተጫወተው ታሪካዊ ሚና ልዩ ክብር እና ምስጋና ይገባዋል” ብለዋል በመልእክታቸው።

በመቀጠል የጁንታውን ቡድን አድኖ ለህግ የማቅረብ ተልዕኮ በተቀጣጠለው የድል ስሜት እስከመጨረሻዋ ሰዓት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

መንግሥት በደረሰበት ወሳኝ የድል ምዕራፍ ዜጎችን ከጥቃት የመጠበቅ እና የመከላከል ተግባሩን በጥንቃቄ፣ በንቃት እና በሃላፊነት ስሜት የሚወጣ መሆኑንም ገልፀዋል።

በቀጣይ በትግራይ ክልል እና በአከባቢው ፍፁም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን አስፈላጊውን ሁሉ በመንግስት በኩል ተፈፃሚ ይደረጋል ብለዋል።

በአጭር ሂደት በትግራይ ክልል በጁንታው ቡድን ሴራ የፈራረሱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት እና የማቋቋም እንዲሁም በሂደት በክልሉ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የማረጋገጥ ስራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል።

“በጠንካራ የአመራር ጥበብ የተመራው ህግ የማስከበር እርምጃችን መሪ ዓላማ የጁንታውን ቡድን ካለበት ለቅሞ ለህግ ማቅረብ ተልዕኮ በመሆኑ፤ አሁንም እስከመጨረሻው ድረስ ለዓላማው የተሟላ ተፈፃሚነት የትግራይ ክልል ህዝብ ወንጀለኞችን ከተደበቁበት ፈልፍሎ የማጋለጥ ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.