Fana: At a Speed of Life!

በሀገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩ የጦር መኮንኖች ቤት በተደረገ ብርበራ በግለሰቦች እጅ መያዝ የሌለባቸዉ የጦር መሳሪያዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩ የጦር መኮንኖች ቤት በተደረገ ኦፕሬሽንና ብርበራ በግለሰቦች እጅ መያዝ የሌለባቸዉ የጦር መሳሪያዎች ተያዙ።

ከሀዲ ጁንታዉ የህዉሃት ቡድን እንደ ሀገር ብጥብጥና ቀውስ ለማድረስ አልሞ ረጅም አመታት በመዘጋጀት ጥቃት ማድረስ ከጀመረበት እለት አንስቶ በተደረጉ ፍተሻዎችና ብርበራዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የተለያዩ የጦርመሳሪያዎች መያዛቸዉን የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በዚህም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሀገር ክህደት ተጠርጥረዉ በእስር ላይ የሚገኙ የጦር መኮንኖች ቤት በተደረገ ፍተሻ ከፋተኛ ጉዳትና ኪሳራ ማድረስ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎች የጦር ሜዳ መነፀሮች፣ ጅፒኤስ፣ በሳተላይት የሚሰሩ ስልኮች፣ ቦንቦች፣ክላሽንኮቭ፣ብሬን፣ለእኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ የሚውሉ የተቀየረው የሰራዊቱ የደንብ ልብስ እና ሌሎች በግለሰብ እጅ መያዝ የሌለባቸዉ መሳሪያዎች በፍተሻ ሊያዝ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

ፍተሻው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችና የሀገሪቱ ቦታዎች የተካሄደ ሲሆን የተያዙ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎቹ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች ሽብር ለመፍጠርና ሀገርን ለማበጣበጥ ጁንታዉ የህወሓት የጥፋት ቡድንና ተላላኪዉ የኦነግ ሼነ ሊጠቀሙባቸዉ እንደነበር እንደተደረሰበት ነው የተገለፀው።

በመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በነበሩ ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ ከተቋሙ ወደ ግለሰቦች እጅ እንዲገቡ የተደረጉ መሳሪያዎች ባይያዙ በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ቀውስ ያስከትሉ እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡

በተደረገዉ ኦፕሬሽንና በህብረተሰቡ ጥቆማ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዉ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ መረጃ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.