Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እና ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው-ጠ/ሚ ፅህፈት ቤት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት እና ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

መንግስት በትግራይ ክልል ህግን የማስከበር እርምጃ መውሰድ በጀመረበት ወቅት በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ የከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ኮሚቴ ማዋቀሩን ነው ፅህፈት ቤቱ የገለፀው።

ይህ ኮሚቴም የህወሃት ቡድን አባላት ለፍትህ ለማቅረብ በተወሰደው እርምጃ በቀጥታ ጫና ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በብሄራዊ  እና በአጋር ድርጅት በኩል የሚገኙ የሰብዓዊ ድጋፎችን የማሰባሰብ እና የማሰራጨት ስራ ሲያከናውን መቆየቱ ተጠቁሟል።

ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ማድረጉን ተከትሎ የመጀመሪያው ዙር ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች በፌዴራል መንግስት በኩል እንዲሰራጭ መደረጉን ፅህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የህወሃት ቡድን ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በነበሩባቸው አካባቢዎች ለተወሰነ ጊዜ የሰብዓዊ ድጋፉ መዘግየቱን ያስታወቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መቐለ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ግን ይህ ሁኔታ መለወጡ ተገልጿል።

የመጀመሪያው ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ ወደ ዳንሻ፣ ወልቃይት ፣ቃፍታ ሁመራ እና ደባርቅ አካባቢዎች መሰራጨቱ ተጠቁሟል።

ህዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም 18 ሺህ 200 ኩንታል የምግብ ድጋፍ የያዙ 44 ካባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ለማሰራጨት ወደ ሽረ መላካቸው ተነግሯል።

በተመሳሳይ 5 ሺህ 500 ኩንታል የምግብ ድጋፍ ወደ አላማጣ፣  7 ሺህ ኩንታል ዱቄት እና  12 ሺህ 500 ኩንታል የምግብ ድጋፍ  ወደ መቐለ እንደተላከ ነው ፅህፈት ቤቱ ያስታወቀው።

እንዲሁም በሶስት ከባድ ተሽከርካሪዎች የህክምና አቅርቦቶች መቐለ መግባታቸው የተገለጸ ሲሆን በነገው ዕለት እንደሚሰራጩ ተነግሯል።

ወደ ሽረ እና አዲግራት ከተሞችም በሰባት ከባድ ተሽከርካሪዎች የህክምና አቅርቦቶች መሰራጨታቸው ተጠቁሟል።

ከዚህ ባለፈ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሰብዓዊ ድጋፎችን በትግራይ ክልል ለዜጎች ለማቅረብ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ስምምነት መፈረሙን  የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.