Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት የአመቻቾች ስልጠና ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስቴር በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት፣ ሀገራዊ መግባባትና አብሮነትን ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ማሕበራዊ መስተጋብሯ የተሟላ ሰላሟ የተጠበቀና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን በማለም የተቋሙን ተልዕኮዎች ለማሳካት ለብሄራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መከበር የማይተካ ሚና ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ አሳታፊ ፕሮግራሞች ተቀርጸው እየተተገበሩ ይገኛል።

ወጣቱ በስብዕና፣ በአመለካከት እና በስራ ባህል ግንባታ ላይ ያለው ሚና እና ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል።

ይህን ለማሳደግም የሰላም ሚኒስቴር የብሄራዊ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ፕሮግራም ቀርፆ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለተፈጻሚነቱ እየተንቀሳቀሰ ይገኛልም ነው የተባለው፡፡

ስለሆነም የብሄራዊ በጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ፕሮግራምን ለማስፈፀምና ፕግራሙ የሚያሳትፋቸውን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ለማሰልጠን የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የተመረጡ 260 ወጣቶች የሚሰለጥኑበት መድረክ ተጀምሯል፡፡

በስልጠናው ከመላው የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡና በፈቃደኝነት የተመዘገቡ የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ስራ ላይ ያልተሰማሩ 50 ሺህ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል፡፡

ለፕሮግራሙ የገንዘብ፣ የግብዓትና የሰው ኃይል ድጋፍ በማድረግ የሀገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ አጋሮች ተሳትፎ መገኘቱን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.