Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎቿን የመደገፍና መልሶ የማቋቋም ዝግጁነት አላት – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎቿን የመደገፍና መልሶ የማቋቋም ዝግጁነትና ብቃቱ ያላት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በህወሓት ቡድን ተፈጥሮ በነበረው ችግር ተፈናቅለው በሱዳን የሚገኙ ሠላማዊ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ተሰደው በሱዳን ከሚገኙት 40 ሺህ ያህል ዜጎች መካከል ከህወሃት ጁንታ ጋር የወንጀል ተሳተፎ ያላቸው ካሉ የመለየት ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ሰላማዊ ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰው የሚቋቋሙ መሆኑንም አመልክተዋል።

ቀደም ሲል የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን ጨምሮ ተፈናቅለው በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህን ለማድረግ የሚያስችል በቂ ልምድ ያላት በመሆኑ በራሷ አቅም ለመከወን የሚያስችል ዝግጅት እንዳላት አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል።

በክልሉ እየተሰሩ ባሉ የሰብዓዊ ድጋፎች 70 በመቶ የሚሆነውን ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግስት እያከናወነ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

በሰብዓዊ ድጋፉ መድሃኒት፣ ምግብ የጫኑ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ የተለያዩ ከተሞች ተጓጉዘው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመቀሌ ከተማ በመገኘት ከመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት ማድረጋቸውም በክልሉ ሰለማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።

በክልሉ አዲስ የተዋቀረው ጊዜዊ አስተዳደር መልሶ አካባቢውን ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ምክክር እያደረገ እንደሚገኝና የመብራት፣ ስልክ እና የአየር ትራንፖርት መጀመር ሠላማዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአንዳንድ አለም አቀፍ ተቋማትና ግለሰቦች “ሰላም የለም” በሚል የሚነዛው የሀሰት ወሬም ግርግር ከመፍጠር ለማትረፍ መሆኑን አብራርተዋል።

እነዚህ አካላት ከጁንታው ጋር የጥቅም ግንኙነት ስላላቸው እኩይ አላማቸውን ለማስፈፀም ሲሉ እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.