Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ከመቸውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ።
 
በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቁ ባለሀብቶቹ ተግዳሮት በሆኑባቸው ጉዳዪች ላይ ኢ/ር ታከለ ኡማ በዘርፉ ከተሰማሩ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች እና ሌሎች ዘርፉ ከሚመለከታቸው ባለድሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል።
 
በውይይቱ ላይ በአራዳ፣ በቂርቆስ እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች ላይ የሚገኙ ከባለ አንድ ወለል እስከ እስከ ባለ 10 ወለል ፎቆች ህንፃዎች ባሏቸው 17 ሳይቶችን መነሻ ያደረገ መነሻ ጥናት ቀርቧል።
 
በጥናቱም በገንቢው፣ በመንግስት መዋቅሩና በባንኮች ላይ ያሉ ችግሮች ህንፃዎቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ተግዳሮት ሆነው መቆየታቸው ተነስቷል።
 
አሁን ላይም በከተማዋ ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ የሚሆኑ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ህንፃዎችም እንዳሉም በመድረኩ ተገልጿል።
 
የውይይቱ ተሳታፊዎች የባንክ ብድር አቅርቦትን ጨምሮ ከሊዝ አዋጅና መመሪያ እ የመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር እንዲሁም ሌሎች ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮችን በዋናነት አንስተዋል።
 
ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወኑ ግንባታዎቹ የመዲነዋ አንጡራ ሃብት መሆናቸው ተናግረዋል።
 
በግንባታው ዘርፍ የሚስተዋለውን ችግሮችን ለመቅረፍም የከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑን ነው የገለጹት።
 
ለዚህም በከንቲባ ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት መሬት አስተዳደር፣ ግንባታ ፈቃድ፣ ፕላን ኮሚሽን፣ መንገዶች ባለስልጣን፣ ኮንስትራክሽን ቢሮ እንዲሁም ከመሠረተ ልማት አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት ያሉ ችግሮችን በግንባታ ስፍራዎቹ በመገኘት እልባት የሚሰጥ ቡድን አንደሚቋቋም አስታውቀዋል።
 
ቡድኑ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑም ተመላክቷል።
 
በትዝታ ደሳለኝ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.