Fana: At a Speed of Life!

በኮንሶ፣ ኩሱሜና ደራሼ ብሔረሰቦች መካከል ግጭት በማስነሳት ከ11 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉና የሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ያደረጉ ተከሳሾች በ19 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮንሶ፣ኩሱሜ እና ደራሼ ብሔረሰቦች መካከል ግጭት በማስነሳት ከ11 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ እንዲሁም የሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ያደረጉ ተከሳሾች በ19 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ።

በጽኑ እስራት እንዲቀጡ የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርባ ምንጭና አካባቢው ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ህዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በሰባት ግለሰቦች ላይ ተደራራቢ ክስ አቅርቦ ነበር።

ክሱ ቀርቦባቸው የነበሩ 1ኛ አበበ አያኖ፣2ኛ ከበደ አርሳይዶ፣ 3ኛ ግርማ ባንሶ፣ 4ኛ በቀለ ባልቻ፣ 5ኛ አባተ ዱቡ፣ 6ኛ ታምሩ ዳጋቴ እና 7ኛ ወገኔ ጋሃኖ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

ቀርቦባቸው በነበረው አንደኛው ክስ ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ነበር።

በዚህም ተከሳሾቹ ለጊዜው እጃቸው ካልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረውን የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ጋር በተገናኘ መነሻ በማድረግ በኮንሶ፣ኩሱሜና ደራሼ ብሔረሰብ መካከል ለግጭት በማነሳሳትና በመቀስቀስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸው በክስ ዝርዝሩ ተጠቅሷል።

በተለይም በየካቲት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ከረፋዱ 4:00 አካባቢ በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ጋቶ ቀበሌ፣በኮንዞ ዞን ሰገንና ካራት ዙሪያ ወረዳ፣ገርጩና አይሎታ ደከቱ ቀበሌዎች መካከል የሚገኝ ቱርባ ኮልባ አልባጮ የተባለ ለም የእርሻ ማሳዎች መነሻ አድርገው ባስነሱት የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ በመሳተፍ መንደር ሁለት ወደ ሚባል አካባቢና ወደ ሌሎች የገጠር አካባቢዎች የእርስ በርስ ግጭቱን ማስፋፋታቸውን ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።

ባስነሱት ግጭት በመሳተፍ ከሚያዚያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ገጀራ፣ቆንጨራ እና የተለያዩ የጦር መመሪያዎ ችን በመያዝ የጋቶ ቀበሌና የሌሎች ነዋሪ የነበሩ 10 ሰዎች ላይ ጥቃት በመክፈትና ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡

በዚህም 864 ሚሊየን 142 ሺህ 575 ብር ከ 57 ሳንቲም የሚገመቱ የመንግስት፣የህዝብና የግለሰብ ንብረቶች ላይ ጉዳት በማድረስና 11 ሺህ 624 ሰዎችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው ተጠቅሶ በዝርዝር ክሱ ላይ ተመላክቷል።

ዐቃቤ ሕግ በሌላኛው ክሱ ደግሞ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በሚያዚያ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት አካባቢ በጋቶ ቀበሌ መንደር 1 ጤና ጣቢያ አካባቢ ይዘውት በሚንቀሳቀሱት የጦር መሳሪያ ተጠቅመው የጋቶ ቀበሌ ቀጠና 9 አመራር የነበረ አስማረ ዳጉ የተባለ ግለሰብን በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በደራሼ በመንደር አንድና በመንደር ሁለት ተከስቶ የነበረ የእርስ በርስ ግጭትን ቅራኔ የነበራቸው ነዋሪዎችን በሚያዝያ 2 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ የእርቅ ሥነ-ስርዓት ላይ ሽማግሌ ሆኖ በማስታረቅ ሚና የነበረው ወንጃላ ከፒኖ የተባለ ግለሰብን ለምን ዕርቅ እንዲፈጸም አደረክ በማለት በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጋቸውን ተጠቅሶ በግድያ ወንጀል ተከሰዋል።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ከ10 በላይ የሰው ምስክሮች በችሎት አቅርቦ አሰምቷል፡፡

ተዘዋዋሪ ችሎቱ በተከሳሾች ላይ የተሰሙ የምስክሮችን ቃል እና ተያያዥ የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በክሱ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ማረጋገጡን ጠቅሶ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

በተሰጠው ብይን መሰረት ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክሮችን ያቀረቡ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ግን በተገቢው መከላከል አለመቻላቸው ተገልጾ አምስት ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ከእነዚህ ተከሳሾች ጋር አብረው ተካተው የነበሩ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸውን ክስ በተገቢው የተከላከሉ መሆኑን ገልጾ በነጻ አሰናብቷቸዋል።

ከዚህም በኋላ ተዘዋዋሪ ችሎቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን በመያዝ ጥፋተኛ የተባሉትን ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.