Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፎ የሚሰጥ ውይይት ፈጽሞ አላደረገችም፤ ወደፊትም አታደርግም- የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በትናንትናው እለት የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች እና የልዑካን ቡድኖቻቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከአውሮፓውያኑ ጥር 13 እስከ 15 ቀን 2020 በዋሽንግተን ዲሲ ሲያካሂዱት የነበረው ውይይት በጥሩ ውጤት መጠናቀቁ ተገልጿል።

የውይይቱን ውጤት እና የኢትዮጵያን አቋም አስመልክቶ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም  ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ትናንት በተደረገው የመግባቢያ ነጥብ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፎ የሚሰጥ አንዳችም ውይይት ፈጽሞ እንዳላደረገች እና ይህም ወደፊትም የኢትዮጵያ ቀዳሚው መርህ ሆኖ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ግድቡ በተመለከተ የሚደረጉ ድርድሮች እና ውይይቶች ኢትዮጵያ ሌሎች ግድቦችን የመገንባት መብቷንም የማይጋፋ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ለውይይቱ መጓተት እንደምክንያት ሲነሳ የነበረውን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ግድቦች የማያያዝ ሁኔታ እንዲቀር ማድረግ ተችሏል ያሉት ተደራዳሪዎቹ፥ የግድቡ ግንባታ በአሁኑ ወቅት በተጠናከረ ሆኔታ መቀጠሉንና ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በመንግስት በኩል ከፍተኛ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንዳለ መሆኑን አመልክተዋል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር የቱሪዝምና የአሳ እርባታ ልማቶች እንደሚኖሩት ገልጸዋል።

የቴክኒክ ውይይቱ ብሎም ከህግ ጋር የሚያያዙት ጉዳዮች አሁንም በዘርፉ ልምድና ክህሎቱ ባላቸው፣ በሐገር ፍቅር እንዲሁም በከፍተኛ ኃላፊነት ብቁ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተመራ ነው ብለዋል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ስም በከፍተኛ ደረጃ በበጎ የሚያሳድግ፣ የመደራደር አቅም እና ተደማጭነትን እንደሚያጎለብትም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ትክክለኛና በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም እስካላት ድረስ የውይይት ቦታው ተጽእኖ አያሳድርባትም ብለዋል።

በያዝነው ዓመት መጨረሻ ግድቡን ውሃ መሙላት እንደሚጀምር እና በዚህም መሰረት ሙሌቱ በጥቅሉ ከ4 እስካ 7 ዓመት እንደሚጠናቀቅ እንደሚጠነቃቅ ነው ያመለከቱት።

እየተደረገ ያለው ውይይት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ሳይሆን የአባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር በትብብር ማደግ ከሚለው የኢትዮጵያ አቋም በመነሳት እንደሆነ በመግልጫው ተመልክቷል።

ከግድቡ ጋር በተያያዘ በተለይ ኢትዮጵያውያን የመገናኛ ብዙሃን አባላት፣ ተንታኞች፣ አክቲቪስቶች እና ሌሎች ጸሃፊዎች የሚያቀርቧቸው መረጃዎች ሚዛንን የጠበቁ፣ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም የሚገነቡ፣ ከአሉባልታ ይልቅ በጥልቅ መረጃ የታገዙና የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ላይ ተጨማሪ ጉልበት የሚሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ግድቡ ላይ አሉታዊ ጥርጣሬ እንዲኖራቸው ሳይሆን ትክክለኛውን መረጃ እንዲያውቁ ድጋፋቸውም የበለጠ እንደጠናከር በማደረግ ረገድ የበኩላቸውን ከፍተኛ ሚና እንዲወጡ ተደራዳዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.