አየር መንገዱ በኩዌት 2020 አቪየሽን ሾው ላይ እየተካፈለ ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩዌት እየተካሄደ ባለው 2020 አቪየሽን ሾው ላይ እየተካፈለ ነው።
አየር መንገዱ በኩዌት ከሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ነው እየተሳተፈ የሚገኘው።
በኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተካሄደ በሚገኘው አቪየሽን ሾው ላይ፥ 37 ሃገራት፣ 200 ድርጅቶች እና ከ70 በላይ የሚሆኑ የንግድ እና የጦር አውሮፕላኖች የአውሮፕላን ትርዒት አሳይተዋል።
አየር መንገዱም ከኤምባሲው ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ባህል፣ የቱሪዝም መስህቦች፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ የባህል አልባሳትና ባህላዊ ቅርጻ ቅርፆች እና የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓቱን ለተሳታፊዎች አስተዋውቋል።
ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎችና አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ ባለሃብቶች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።