በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ጀማል አል ዲን ኡመር መሀመድ ኢብራሂም ጋር በካርቱም ተወያዩ።
በውይይታቸው በድንበር ፀጥታ ዙሪያ መክረዋል።
የሁለቱን ሀገራት የድንበር ላይ የጋራ ጠባቂ ሀይልን በፍጥነት በማደራጀት በጋራ ወንጀሎችን መካላከል የሚቻልበትን ሁኔታ ተመልክተዋል።
በተለይም በድንበር ላይ የሚከናወኑ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችንም መግታት ስለሚቻልበት ሁኔታም መመካከራቸውን የሱዳን የዜና አገልግሎት/ሱና/ ዘግቧል።
የድንበር ላይ የፀጥታ ቁጥጥር ስራውንም ለማጠናከር የሀገሪቱ የፀጥታ ቡድኖች በቀጣይ እየተገናኙ መወያየት እንደሚገባቸውም ተመልክተዋል።
አምባሳደር ሽፈራው የሁለቱን ሀገራት የድንበር ላይ ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ የጋራ ኮሚሽናቸውን በመከላከያ ሚኒስትሮች ደረጃ ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለሱዳን የፖለቲካ መረጋጋት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ያረጋገጡ ሲሆን፥ አሜሪካ ሀገሪቱን ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ ብላ ካስቀመጠቻቸው ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ሱዳንን እንድታስውጣ ጥረቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።