Fana: At a Speed of Life!

ለመኸር እርሻ የሚውል ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2013 እና 2014 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ የሚውል ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ ለ2013/14 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ የሚውሉ እንደ የሰብል ምርጥ ዘርና አግሮ ኬሚካሎች ያሉ የግብርና ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።

በምርት ዘመኑ ከ18 ሚሊየን 169 ሺህ በላይ ኩንታል ዩሪያን ጨምሮ የተለያዩ የማዳበሪያ አይነቶችን ከውጭ ለማስገባት ያቀደው ኮርፖሬሽኑ፥ ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ከ15 ሚሊየን 47 ሺህ በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ማድረስ መቻሉን አመልክቷል።

ከዚህ ውስጥ 12 ሚሊየን 127 ሺህ 510 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ በሕብረት ሥራ ማህበራት አማካይነት ለአርሶ አደሩ እየተከፋፈለ መሆኑን አስታውቋል።
ቀሪው ከ6 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ በቀጣይ ጊዜ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባም ነው የተገለጸው።

በምርጥ ዘር አቅርቦትም እስካሁን 284 ሺህ 437 ኩንታል የተለያዩ የዘር ደረጃቸውን የጠበቁ የሰብል ዘሮችን በኮርፖሬሽኑ እርሻዎች፣ በሰፋፊ የባለሃብቶች እርሻና በአርሶ አደሮች ማሳ በማምረትና በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች እየተከፋፈለ ይገኛል ተብሏል።

በተመሳሳይ በሰብል ዘመኑ በኮርፖሬሽኑ እርሻዎች፣ በባለሃብቶች እርሻና በአርሶ አደሮች ማሳ 335ሺህ 765 ኩንታል ተጨማሪ የተለያዩ የሰብል ዘሮችን ለማምረት ታቅዶ መሬት የማዘጋጀትና ዘር የመዝራት ሥራ እያካሄደ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

በዚሁ የዝግጅት አካል ለ2014/15 የሰብል ዘመን ለተጠቃሚዎች ዘር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ19 በላይ የተለያዩ የሰብል ዘሮችና 80 የሚጠጉ ዝርያዎችን በተለያዩ የዘር ደረጃዎች ማባዛቱም ነው የተጠቀሰው።

በተጨማሪም የመነሻ ዘሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ዘር የማባዛትና የማሰራጨት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ ኮሙኒኬሽንና ማህበራዊ ጉዳዮች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም አስታውቀዋል።

ከአግሮ ኬሚካል አቅርቦት አኳያም ኮርፖሬሽኑ የፀረ-አረም፣ የፀረ-በሽታ፣ የፀረ-ተባይና የፀረ-መጋዘን ነፍሳት ተባዮች ኬሚካሎች እንዲሁም በሰው ኃይል የሚታዘሉ የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችን ከውጭ በማስገባት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ መሆኑን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.