የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የእሳት ስርዓት አያያዝ ዕቅድ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ከእሳት አደጋ መከላከል የሚያስችል የእሳት ስርዓት አያያዝ ዕቅድ ለማጽደቅ የመጨረሻ ግምገማ ተካሄደ፡፡
በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ከአፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀው ሰነድ ግምገማ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡
እቅዱ በግምገማ መድረኩ በተሰጡ አስተያየቶች ዳብሮ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ይህ እቅድ በኢትየጵያ የፓርኮች የእሳት ሥርዓት አያያዝ ሲዘጋጅ ከቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ቀጥሎ ሁለተኛው መሆኑን ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ስርዓቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የእሳት አደጋዎችን የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል ሰነዱን ያዘጋጁት ዶክተር ምናሴ ጋሻው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና ሌሎች በተመሳሳይ ሂደት መሰል የእሳት ስርዓት አያያዝ ዕቅድ እንደሚዘጋጅላቸው ተመላክቷል፡፡