Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል መንግሥት የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በጀት  መያዙ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የፌዴራል መንግሥት የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በጀት መያዙን  የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ።

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ቴክኒክ ኮሚቴ አባል አቶ በትግሉ ተስፋዬ ÷በቻግኒ ራንች ጊዚያዊ መጠለያ የነበሩ ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ ተመልሰዋል ብለዋል፡፡

ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ዜጎችም እስከ አሁን ድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብና ቁሳቁስ በማቅርብ ቀና ትብብር እንዳደረጉላቸው ጠቁመው÷ አሁን ላይም ረጂ ድርጅቶችና መንግሥት ለተፈናቃዮቹ ዕለታዊ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ለተፈናቃዮች የዕለት ምግቦችን ከማድረስ ጎን ለጎን የአካባቢው ባሕልና ሥነ ሥራዓት በሚፈቅደው መሠረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት የእርቀ ሰላም ሥነ-ስርዓት መደረጉን አቶ በትግሉ ተናግረዋል፡፡

እርቀ ሰላሙ በነዋሪዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠርና ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ ያስችላል ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ተረጋግተው እንዲኖሩ በጸጥታ ኀይሎች ጥበቃ እየተደረገላቸውና ምንም አይነት የፀጥታ ስጋት አለመኖሩን አቶ በትግሉ አስረድተዋል፡፡

ለተፈናቃዮቹ የመጠለያ፣ የመጸዳጃ ቤት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃና የሕክምና አገልግሎት እንደተሟላላቸውም ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት በዳንጉር፣ በቡለን፣ በድባጤና በማንዱራ ወረዳዎች መኖር ጀምረዋል ÷ በተፈናቃዮች ማዕከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለእርሻ ልማት የሚውሉ ትራክተሮችን በማቅረብ ማልማት መጀመራቸውንም አቶ በትግሉ  ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከማንዱራ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ወደ መደበኛ ሥራቸው ለመመለስ የሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡

በቀጣይ ዜጎች በዘላቂነት እስከሚቋቋሙ ድርስ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት የጋራ ግብረ ኀይል ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ሥራውን ለማሳለጥ ሲባል በመተከል ዞን የጋራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ይቋቋማል ብለዋል፡፡

የሚቋቋመው ጽሕፈት ቤት ተፈናቃዮች ወደ መደበኛ ሥራ እስከሚገቡ ድርስ ችግሮቻቸውን እየተከታተለ ይፈታል፣ ማስተካከያ ርምጃም ይወስዳል ነው ያሉት፡፡

“የፌዴራል መንግሥትም የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በጀት መድቧል” ብለዋል፡፡

ይህም ተፈናቃዮቹ መደበኛ ሕይወት መኖር እንዲጀምሩ ይደግፋቸዋል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

 

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.