Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በስልክ ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቹንግ ኢዩ ዮንግ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የስልክ ውይይት አድርገዋል።

በዚህ ወቅትም በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አቶ ደመቀ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በተፈጠረ ሁኔታ የሰብዓዊ ተግባራት ለማሳለጥና የክረምት ወቅት በመሆኑ ማህበረሰቡም የእርሻ ሥራውን ተረጋግቶ እንዲያከናውን የተናጥል የተኩስ አቁም ማወጁንም ተናግረዋል።

ይህ የመንግሥት እርምጃ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሲነሳ የነበረን ስጋት በመቅረፍና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ አካላት ሥራቸውን በተመቻቸ ሁኔታ እንዲሰሩ ለማስቻል ሊረዳ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በኢትዮጰያ ለሰብአዊ ድጋፍ ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያ 6ኛውን ሃገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ማካሄዷን ጠቁመው በአሁኑ ወቅትም የምርጫ ውጤቱ እየተጠበቀ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የደቡብ ኮሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቹንግ ኢዩ ዮንግ በበኩላቸው የሁለቱን ሃገራት ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊነትን በማስቀደም በተናጥል ያወጀውን የተኩስ ማቆም ውሳኔ እንደሚደግፉ ገልጸውላቸዋል።

በተጨማሪም በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ ያካሄደችው ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አያይዘውም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና በዓለም አቀፍ መድረኮች በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.