Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶክተር አኔቴ ዌበር ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሯ በሀገሪቱ እየተካሄደ ስላለው ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ የምክክር ሂደት እና እያስገኘ ስላለው ዘርፈ ብዙ ውጤት ገለጻ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ከሰብዓዊ አጋሮች ጋር በትብብር ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እየተሳለጠ ያለበትን አግባብ እና ወደክልሉ እየተላከ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ መጠን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም መንግስትን ጨምሮ በተለያዩ የሰብዓዊ እርዳታ አካላት ትብብር ለሁለት ወራት ገደማ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የሚያዳርስ የምግብ ፍጆታ ክምችት በክልሉ መቀመጡን አስረድተዋል።

ከሰብዓዊ ተኩስ አቁም ውሳኔው በኋላ 1974 ነጥብ 6 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና 1 ሺህ 875 ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እንዲሁም 90 ሺህ 294 ሊትር ነዳጅ በሁለት ዙር በሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮች አማካኝነት መንግስት ለክልሉ ህዝብ ልኳል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ገበሬዎች የእርሻ ስራ እንዳይስተጓጎል በቂ የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር ክምችት መንግስት በክልሉ ማስቀመጡንም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶክተር አኔቴ ዌበር በበኩላቸው ውይይቱ በርካታ ግልጽ ያልነበሩ ጉዳዮችን ያስገነዘባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች እያደረጉ ላለው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.