Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው የህውሃት ቡድን በዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊጠየቅ ይገባል- ትዴፓ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህውሃት ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ በመሆኑ በዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ያስታወቀው፡፡
ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪ ቡድኑ በትግራይ ክልል እየፈጸመ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በአግባቡ እንዲረዳ ማድረግ ተገቢ መሆኑም ተጠቁሟል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሌ፤ አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያ በማድረግ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው መሆኑን ገልጸዋል።
ቡድኑ እታገልለታለሁ እያለ ለሚያወራለት ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት ሃላፊነት እንዳማይሰማው ጠቁመው፤ ይህንንም በተደጋጋሚ በፈጸማቸው እኩይ ተግባራት በግልጽ ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።
ቡድኑ ከስልጣን ከወረደ በኋላ ግን የሚፈጽመው ግፍና በደል እየከፋ መምጣቱንም አቶ ሙሉብርሃን ተናግረዋል።
ቡድኑ “ለህዝብ እታገላለሁ ቢልም የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ከማድረግ ባለፈ ህጻናትና አቅመ ደካሞችን ጭምር በጦርነት በማሳተፍ ጸረ-ህዝብነቱን በተግባር እያስመሰከረ ነው” ብለዋል።
ይህም ቡድኑን በዓለምአቀፍ ህግ በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቀው መሆኑን ጠቁሟል።
የፌዴራል መንግስት ለህዝቡ በማሰብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ የትግራይ አርሶአደር በአግባቡ እንዳይጠቀም እንቅፋት የሆነው አሸባሪ ህወሓት መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ አሸባሪ ቡድኑ መላ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ህዝቡ እንዲደግፈው የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
“የትግራይ ህዝብ አሸባሪው ህወሓት በድጋሚ ስልጣን ላይ ይመጣል በሚል በቀቢጸ-ተስፋ ሊጠብቅ አይገባም” ያሉት ሃላፊው፤ ቡድኑ እስኪከስም ድረስ ከሽብር ድርጊቱ እንደማይቆጠብ ተናግረዋል።
መንግስት የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር በጥንቃቄ መመከትና የትግራይን ህዝብ ነጻ ማውጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያውያን ተጋሩ ሲቪክ ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሃንስ ጎይቶም በበኩላቸው፤ መንግስት ለትግራይ ህዝብና ለአርሶአደሩ የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የአሸባሪው ህውሃት ታጣቂዎች በክልሉ ከፍተኛ ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን አድርገዋል።
ከዚህ ውስጥ በክልሉ ህጻናትና አቅመ ደካማ አረጋውያንን ለጦርነት ከማሰለፍ ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን በመልቀቅ ዝርፊያና ህገ-ወጥ ተግባር እንዲበራከት ማድረጉን አንስተዋል።
በትግራይ ህዝብ ላይ የሚከሰቱ ግፍና መከራዎች መነሻ አሸባሪው የህወሃት ቡድን መሆኑን ጠቅሰው፤ ቡድኑ ከዓለምአቀፍ የጦር ወንጀለኝነት ባለፈ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የትግራይ ህዝብም ቡድኑ ለረጅም ዓመታት ሲያደርስበት የነበረውንና አሁንም እያስከፈለው ያለውን ዋጋ በአግባቡ በመረዳት ይህን ሃይል ታግሎ ነጻ መውጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አይቶ እንዳላየ ማለፉ ተገቢ አለመሆኑን አብራርተዋል።
ቡድኑ በተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ የውጭውን ማህበረሰብ ለማሳሳት የሚያደርገው ሙከራም በእውነተኛ መረጃ ሊከሽፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አቶ ሙሉብርሃን በበኩላቸው ቡድኑን በእውነተኛ መረጃ ለማጋለጥ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ምንጭ፡- ኢዜአ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.