Fana: At a Speed of Life!

የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በመሳተፋቸው በተሽከርካሪ ይደርስ የነበረ አደጋ መቀነሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በትራፊክ ማስተናበር ስራ ላይ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች በተሽከርካሪ ይደርስ የነበረ አደጋ መቀነሱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገለጸ።

ቢሮው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመሆን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ኢንጅነር ብርሃኑ ግርማ እንዳሉት÷ የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በትራፊክ ማስተናበር ስራ ላይ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች በተሽከርካሪ ይደርስ የነበረው አደጋ ቀንሷል።

በተሽከርካሪ አደጋ የሚጠፋውን የሰው ልጅ ሕይወትና የኢኮኖሚ ኪሳራ ለመቀነስ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበኩሉን አስተዋጾ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

”በበጎ ፈቃድ የሚሰራው ስራ ለራሳችንና ለወገናችን ነው” የሚሉት ኢንጅነር ብርሃኑ÷ ሁሉም ለስራው ትብብር ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል።

ካለፈው አራት ዓመት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመሆን በ2009 ዓ.ም በ100 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የተጀመረው ስራ በየጊዜው ለውጥ እያሳየና ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱን ተናግረዋል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት “በከተማዋ እያደገ መጥቷል” ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ ናቸው።

በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በተለያዩ ሙያዎች አገልግሎት ላይ እየተሳተፉ ነው።

ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚውል ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማሰባሰብ መቻላቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በዚህ ዓመት በበጎ ፍቃድ ስራው ከ2ነጥብ 8ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞች ለማሳተፍ ታቅዶ ከ3 ሚለየን በላይ መሳተፋቸውን ሃላፊው ገልጸዋል።

በበጎ ፍቃድ ስራም ባለሀብቶች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ በዚህም “ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው” ብለዋል።

የክረምት በጎ ፍቃድ ስራ ከተጀመረ ሁለት ወራት እየተጠጋው ሲሆን÷ እስከ አሁን በ19 መርሃ ግብሮች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰሩ ይገኛሉ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.