Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ-19 ክትባት በህገ ወጥ መንገድ ሲገበያዩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮቪድ-19 ክትባት በህገ ወጥ መንገድ ሲገበያዩ የነበሩ 3 ተጠርጣሪዎች ከነ ኤግዚቢቱ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
 
ተጠርጣሪዎቹ ነሃሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ ደጃች ውቤ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡
 
አንድ ግለሰብ በህገ ወጥ መንገድ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መድሃኒት በቦርሳ ይዞ ለመሸጥ እየተደራደረ ስለመሆኑ ህብረተሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠቱ እና ፖሊስም ፈጣን ክትትል በማድረጉ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
 
በዚህም ፖሊስ 10 ብልቃጥ የቻይና ሲኖ ፋርም እና 3 ብልቃጥ የአሜሪካ ጆን ኤንድ ጆንሰን የተባሉ የኮቪድ 19 ክትባት መድሀኒቶችን እንዲሁም የክትባቱ መስጫ 12 መርፌዎች እና 3 የማቀዝቀዣ ቁሶችን ግብይቱ ለመፈፀም ሲስማሙ ከነበሩ 3 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ ይገኛል።
 
ክትባቶቹ ከየት ተሰርቀው እንደወጡ ለማወቅ እየሰራ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ ለገበያ የሚቀርቡ መድሀኒቶች በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ከጤና ተቋማት እና ከህጋዊ መድሃኒት መሸጫ መደብሮች ውጪ ማንኛውንም መድሃኒት ገዝቶ ባለመጠቀም ጤናውን እንዲጠብቅ አሳስቧል።
 
ህብረተሰቡ እንዲህ አይነት ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.