የወረታ ደረቅ ወደብ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ) የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ከተማ ያስገነባው ደረቅ ወደብና ተርሚናል የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ አግልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው።
በወደቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ የ3 ሄክታር ግንባታ በጠጠር ንጣፍ የተዘጋጀ የኮንቴነርና የተሽከርካሪ ማስተናገጃ ተርሚናል፣ 500 ሜትር ካሬ መጋዘን፣ የቢሮ ህንፃ፣ የመዳረሻ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የጥበቃ ማማ እና የዙሪያ አጥር ያሟላ ነው።
በተጨማሪም የጥልቅ ውሃ ጉድጓድና የውሃ መፋሰሻ ስርዓት እንዲሁም መጠባበቂያ ጄኔሬተርን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እና ሌሎችም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች አሉት ተብሏል።
ለግንባታው ከ100 ሚሊየን በላይ ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን በአጠቃላይ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የወደብ ማሽነሪዎችን ጨምሮ የቢሮ ቁሳቁሶች የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑን ከኢትዮጵያ የባህር እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።