Fana: At a Speed of Life!

በጉራፈርዳ ወረዳ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ዕርቀ ሠላም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ተከስቶ የነበረውን የሠላምና የፀጥታ ችግር በአካባቢው ባህል መሠረት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የዕርቀ ሠላም ስነ-ስርዓት ተካሄደ።

ባህላዊው የዕርቀ ሠላም ስነ ስርዓት፥ በአካባቢው ማህበረሰብ ባህል መሠረት ደም የተቃቡ ወገኖች ዳግም ወደ ግጭት እንዳይመለሱ እና ወደ ቀድሞ ሰላማዊና የአብሮነት ህይወታቸው ለመመለስ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በጉራፈርዳ ወረዳ አሁን ላይ የተገኘውን ሠላምና አንድነት ይበልጥ ዘላቂነት ባለው መልኩ ማስቀጠል እንዲቻል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባም ሰምምነት ላይ ተደርሷል።

በወረዳው በተካሄደው የዕርቀ ሠላም መድረክ ላይ የተሳተፉ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሰጡት አስተያየት፥ የዕርቀ ሰላሙ ሂደት የቆየውን የህዝባችንን የጋራ ማህበራዊ መስተጋብር ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ከልብ በመነጨ ይቅር በመባባል ዕርቁን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በዕርቀ ሠላም ስነስርዓቱ ላይ ከጫካ የተመለሱ ወጣቶች ባሰሙትቃ “ በተሳሳተ መንገድ ጫካ ገብተን ህብረተሰቡንና መንግስትን በድለናል ከዚህ በኋላ የተገኘውን ሠላም ዳግም ከእጃችን እንዳይወጣ በማድረግ ለመካስ እንሰራለን” ብለዋል።

የጉራፈርዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ሻሎ በዕርቀ ሠላም ስነ ስረዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ በወረዳው በሚገኙ በተለያዩ ቀበሌዎች ከጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በርካታ ነዋሪዎችን ለሞትና ለመፈናቀል፥ እንዲሁም ለንብረት ውድመት ዳርጓል፡፡

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፥ ባለፈው አንድ ዓመት በዞኑ የተለያዩ ጥያቄዎች ሽፋን በርካታ ወጣቶች ጫካ በመግባት ሰፊ የፀጥታ ችግር ሲፈጥሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ችግሩ ለመፍታትና አስተማማኝ ሠላምን ለማምጣት በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የአካባቢውን ሠላምና የማህበረሰቡ የቆየ የአብሮነት ባህል ወደነበረበት እንዲመለስ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ከየቀበሌው የተውጣጡ የሠላም አምባሳደሮች ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተወካይና የፀጥታ ዘርፍ አማካሪው አቶ ኩታዬ ኩስዬ፥ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች በጥፋት ኃይሎች ሴራ ተገፋፍተው ወደ ግጭት በመግባት ለችግር ሲዳረጉ መቆየታቸውን አስተውሰዋል።

የወረዳው ወጣቶችም ራሳቸውን ከእኩይ ተግባር በማግለል የአካባቢው ሠላም በዘላቂነት እንዲመለስ የበኩላቸውን ጥረት በማድረጋቸው አመስግነዋል።

የደቡብ ክልል ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊም፥ በወረዳው እስካሁን በነበረው እንቀስቃሴ ህዝቡ ለሠላምና አብሮነት ካለው ፍላጐት የተነሳ ከፀጥታ ኃይሉ ጐን በመሆን ሌት ተቀን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፥ ህብረተሰቡ አሁን የተገኘውን ሠላም በመጠበቅ ዘላቂ ማድረግ ይጠበቅበታል ማለታቸውን ደሬቴድ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.