Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ቀንድ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ውይይት በበይነ መረብ ተካሄደ፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እንደገለፁት፥ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በትራንስፖርት፣ በንግድ፣ በገጠር ፋይናንስ፣ በመጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠርና የበረሀ አንበጣን በመከላከል ረገድ ተባብረው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ማዕከላዊ ስፍራ የምትገኝና ከሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር የምትዋሰን በመሆኗ ለኢኮኖሚያዊ ትብብሩ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች ነው የተባለው፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት እድገትና ልማትን እውን በሚያደርጉ በመንገድ ትራንስፖርት ትስስር፣ በታዳሽ ሀይል ንግድ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ ትስስር፣ በአርብቶ አደሮች ልማትና በአረንጓዴ ልማት ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና ይኖራታል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ውስጣዊ አለመረጋገትም በህግ ማስከበሩ ሂደት ተወጥታ ፊቷን ወደ እድገትና ልማት በመመለስ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ውጤታማ ኢኮኖሚያዊ ትብብር የምትጫወተውን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል በመድረኩ ተነስቷል።

ከዚህ ባለፈም ለተግባራዊነቱ የመንግስት አካላት፣ የዜጎች፣ የግሉ ዘርፍና የልማት አጋሮች ትብብርና ቅንጅት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የፋይናንስ ሚኒስትሮቹ ምክክር በየሶስት ወራት የሚካሄድ ሲሆን የትናንቱ ምክክር ለዘጠነኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.