Fana: At a Speed of Life!

የክተት ጥሪውን ተቀብለን ለመዝመት ተዘጋጅተናል – የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ሀገርን ለማዳን የተላለፈውን የክተት ጥሪውን ተቀብለው ለመዝመትና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።

መንግስት በሀገር ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ አስመልክቶ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት÷ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ጭምር ኢትዮጵያን ለማዳን እንደተነሳሱ ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ተመስገን አድንቀው÷ ”የሀገርን ህልውና የማስጠበቅ ተግባር ለመንግስትና ለመከላከያ ሰራዊት ብቻ የምንተወው ጉዳይ ባለመሆኑ እያንዳንዳችን ከእኔ ምን ይጠበቃል በሚል እሳቤ ግዴታችንን መወጣት አለብን” ብሏል።

”ሀገሬን ለማዳን እስከግንባር ድረስ በመሄድ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ” ያለው ወጣቱ ÷ በሰሜን ኢትዮጵያ አሸባሪው ቡድን በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት የሁሉም ዜጋ ችግር በመሆኑ እንደ አንድ ቤተሰብ በማሰብ መዝመት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

አሸባሪው ህወሓት ዋነኛ የጦር ስትራቴጂው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመሆኑ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ህዝብን የሚያሸብሩ የተዛቡ መረጃዎችን እንደሚያስተላልፉ ገልጾ ÷ ሁሉም ሰው በአሸባሪው ቡድን የሀሰት መረጃ ሳይደናገር አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ አጠራጣሪ ጉዳዮችን ለፀጥታ አካላት በመጠቆም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አመልክቷል።

ህወሓት በሚያሰራጨው የሀሰት መረጃ ዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ እያሳሳተ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ወደ ህልውና ዘመቻው የገቡት እውነትን ይዘው በመሆኑ ድሉ የኢትዮጵያ ነው ያለው ደግሞ ወጣት አብዱልረዛቅ ሸምሱ ነው።

”በሠላም ሰርቼ የምኖረው ሀገሬ ስትኖር ነው” ያለው ወጣት አብዱልረዛቅ ÷ በሀገር ላይ የተቃጣውን ጦርነት ለመመከት እስከ ግንባር ድረስ ዘምቶ ለመዋጋት መዘጋጀቱን አስታውቋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ስምዖን ከተማ በበኩላቸው ÷ ከዚህ ቀደም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው÷ ”ለሀገሬ የማደርገው ድጋፍ ገንዘብ በመስጠት ብቻ ተወስኖ አይቀርም” ብለዋል።

ግንባር ድረስ በመዝመት ባላቸው የመካኒክነትና የሹፍርና ሙያ ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

”አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ዘመኑ እርስ በአርስ ሲያባላን ቢቆይም ሀገራችንን በመንካቱ ዳግም አንድ የምንሆንበትን ዕድል ፈጥሮልናል” ያሉት አቶ ስምዖን ÷ ቡድኑ ተደምሰሶ ኢትዮጵያ ወደ ሠላሟ እንድትመለስ አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

ነዋሪዎቹ የክተት የጥሪውን ተቀብለው በመዝመት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውንና እስከዚያም ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው እንደሚጠብቁ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.