Fana: At a Speed of Life!

በህልውና ዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊት አባላት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የጉምሩክ ኮሚሽንና የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በህልውና ዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡

ድጋፉን ያደረጉት የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽንና የጤና ሚኒስቴር ናቸው።

የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች በመከላከያ ዋር ኮሌጅ እና በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የመከላከያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን የሰራዊት አባላት ጎብኝተዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ÷ መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የኢትዮጵያን ህልውና እያስጠበቁ ለሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሞራልና የቁሳቁስ እገዛ በማድረግ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ኮሚሽኑ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊቱ አባላት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ሁሉም ዜጋ ሰራዊቱን በመደገፍ ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ÷ ድጋፉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሰራዊቱ ጎን መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ለሀገሩ ህልውና መጠበቅ ዘወትር በታሪክ የሚወሳ ጀብዱ እየፈጸመ መሆኑን ጠቅሰው ÷ በዚህም ትልቅ ክብርና ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

ጉዳት ደርሶባቸው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙት የሰራዊቱ አባላት ከጉዳታቸው አገግመው ዳግም አገራቸውን ከጠላት ለመታደግ ያላቸውን ቁርጠኝነትንም አድንቀዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ÷ ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊቱ አባላት፣ ለጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም የችግሩ ሰለባ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት እርዳታ የመስጠት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል፡፡

ከክልሎችና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሯ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.