Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሬድዋን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የእስያ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የባንግላዴሽ፣ የህንድ፣ የሲሪላንካ፣ የደቡብ ኮሪያ እና የቻይና አምባሳደሮች ጋር በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ የተናጠል ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ከዚህ በፊት ነዋሪነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና ኦሽኒያ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ድርጅት አምባሳደሮች ጋር አጠቃላይ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የዛሬው የተናጠል ውይይት ደግሞ የተሻለ መተዋወቅ በመፍጠር ቀጣይ ስራዎችን በቅርበትና በትብብር ለማከናወን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ ከእስያ ሀገራት ጋር ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ የሁለትዮሽ እንዲሁም የባለብዙ ወገን ግንኙነት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡

ከሀገራቱ ጋር ያለውን በተለይም የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የባህልና የህዝብ ለህዝብ እንዲሁም የትምህርት እና ስልጠና ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ኢትዮጵያ ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኗንም አስታውቀዋል።

የየሀገራቱ አምባሳደሮች በበኩላቸው÷ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በሀገራቸው ያሉ የተለያዩ ባለሀብቶችን እና ኩባንያዎችን ቀልብ የሳበ መሆኑን አንስተዋል።

ዘርፈ ብዙ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከርም ከመቸውም ጊዜ በተሻለ በቅርበት እንደሚሰሩ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.