Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከልና የአርሶ አደሮችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን ለማስቅረትና በከተማዋ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ።

መመሪያውን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ እና የከተማዋ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ኮሚሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በስድስት ክፍለ ከተሞች፣ በአራት ወረዳዎች እና በ306 ብሎኮች አርሶ አደሮች እየኖሩ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።

አርሶ አደሮቹ በቀደሙት ዘመናት ከተማዋ እየሰፋች በሔደች ቁጥር እየተገፉና ተገቢ ካሳ ሳያገኙ መተዳደሪያ የሆነውን መሬታቸውን ይለቁ ነበርም ነው የተባለው።

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚልኬሳ ጃጋማ እንደሚሉት አሁን የተዘጋጀው መመሪያ ቁጥር 20 /2013 ዓ.ም እነዚህን ችግሮች ይፈታል።

የመመሪያው መዘጋጀት ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለማስቀረትና የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሆኑንም አብራርተዋል።

በመመሪያው መሰረትም በራሳቸው ይዞታ ላይ የግብርና ስራ እያከናወኑ ያሉ አርሶ አደሮች ‘የግብርና መጠቀሚያ ሰርተፊኬት’ ይሰጣቸዋል ተብሏል።

አንድ አርሶ አደር ከአጠቃላይ ይዞታው ላይ በ500 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማከናወን እንዲችል በመመሪያው ተቀምጧል።

ከዚህ ጎን ለጎን የአርሶ አደር ልጆች በ150 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የመኖሪያ ቤት መገንባት እንዲችሉም እድል ይፈጥርላቸዋል ነው የተባለው።

ይህ መሆኑ አርሶ አደሩ የባለቤትነት መብቱ ተረጋግጦ በሕጋዊ ይዞታው ላይ በሚመቻውና በቻለው መልኩ መልማት ያስችላል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ በበኩላቸው የግብርና መጠቀሚያ ሰርተፊኬት አስፈላጊው ማጣሪያ ተደርጎ ለትክክለኛው ሰው ይሰጣል ብለዋል።

ሂደቱ በከተማዋ የሚደረገው ልማት ሰው ተኮር እንዲሆንና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ከልማቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላልም ነው ያሉት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.