Fana: At a Speed of Life!

7 ዓመት ጽኑ እስራትና 3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተፈርዶበት የነበረ ግለሰብ በነጻ ተሰናበተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አቡበከር አሕመድ አሊ በተከሰሰበት ከባድ ዕምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል በ7 ዓመት ጽኑ እስራትና 3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤት በነጻ አሰናብቶታል፡፡

ተከሳሹ ከ1998 ዓ.ም እስከ ጳጉሜ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በሃያቴ አክሲዮን ማኅበር የፕሮጀክት ግብዓቶች ማከማቻ ንብረት ክፍል ሆኖ አገልግሏል፡፡

በዚሁ ጊዜም የተረከበውን ንብረት ሳያስረክብ መጋዘኑን ቆልፎ መሰወሩና መጋዘኑ በኦዲተሮች ተከፍቶ የንብረት ቆጠራ ሲከናወን ከተረከበው ንብረት መካከል 1 ሚሊየን 575 ሺህ 525 ብር ከ9 ሳንቲም የሚያወጡ ንብረቶች አጉድሎ ለግል ጥቅም አውሏል ተብሎ በከባድ ዕምነት ማጉደል ሙስና ወንጀል በ2015 ዓ.ም በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦበት ነበር።

በወቅቱ መዝገቡን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳይ ችሎትም የቀረበውን ክስ ተከትሎ ሁለት ኦዲተሮችን ጨምሮ አራት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል በማዳመጥና የቀረቡ ማስረጃዎችን በመመርመር ተከሳሹ በሌለበት በ7 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ችሎቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረትም የፌዴራል ፖሊስ ግለሰቡን አፈላልጎ በመያዝ ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ማስረከቡ ተገልጿል፡፡

ግለሰቡም መከሰሱን እንደማያውቅና መጥሪያ እንዳልደረሰው ገልጾ እራሱን ሳይከላከል በሌለበት የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ እንዳልሆነ በመጥቀስ መዝገቡ በድጋሚ እንዲታይ ለፍርድ ቤቱ ያመለክታል፡፡

አቤቱታውን የተቀበለው ፍርድ ቤትም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በ3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይለት አድርጓል።

ግለሰቡ ጠበቃ የማቆም አቅም እንደሌለው መግለጹን ተከትሎም በፍርድ ቤቱ የመንግሥት ተከላካይ ጠበቃ ድጋፍ እንዲደረግለት በማድረግ የክስ መዝገቡ በዝርዝር ይታያል፡፡

በግለሰቡ ላይ በተመሰረተበት ክስ ላይ የተሰሙ አራት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃልና የሠነድ ማስረጃ በችሎቱ መመርመሩም ተጠቅሷል፡፡

ማስረጃው ከተመረመረ በኋላም 3ኛና 4ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆኑት ኦዲተሮች ከሰጡት የምስክርነት ቃል ያልተጣጣመና ከዚህ አንጻር ኦዲተሮቹ ገለልተኛ ናቸው ብሎ መውሰድ እንደማይቻል በመግለጽ ሌሎቹ 1ኛ እና 2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችም በንብረት ርክክብ ቆጠራ ካልሆነ በስተቀር ጉድለቱን እንደማያውቁና ማን ምን ያህል አጎደለ፣ በገንዘብም ምን ያህል መጠን ጉድለት እንደታየ ያላስረዱ ስለሆነ እና የቀረበው የሠነድ ማስረጃም ዐቃቤ ሕግ ካቀረበው ክስ ጋር እንደማይጣጣም እና ክሱን የሚያስረዳ ማስረጃ ሆኖ አለመገኘቱን ችሎቱ ገልጿል።

በዚህም መሰረት 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በወ/መ/ስ/ህግ ቁጥር 141/1 መሰረት ግለሰቡ መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ሊሰናበት ይገባል በማለት ግለሰቡን በነጻ አሰናብቶታል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.