Fana: At a Speed of Life!

በሚቀጥሉት 10 ቀናት ዝናብ ሰጭ ገጽታዎች በበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪዎቹ አሥር ቀናት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እየተጠናከሩ እንደሚቀፅሉ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

በዚህ መሰረትም በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ፤ በመካከለኛው፣ በምስራቅ፣ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

በመሆኑም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ነው የተገለጸው፡፡

ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፤ ቦረና፤ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ፤ አዲስ አበባ፤ ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞንና የምስራቅ ጎጃም ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡

በተመሳሳይ የአፋር ክልል ዞኖች፤ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፤ የምስራቅ ትግራይ  ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የሱማሌ ክልል ዞኖች ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ የሚያገኙ ይሆናል፡፡

የተጠቀሱት አካባቢዎች በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ አንደሚያገኙ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉባቦር፤ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ የደቡብ እና የሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ የዋግህምራ ዞኖች፣ ከጋምቤላ ክልል የአኛዋክ እና የመዥንግ ዞኖች፤ ከቤንሻንጉል ክልል የአሶሳ፣ የማአኮሞ ልዩ ወረዳ፤ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿል፡፡

በሚቀጥሉት ቀናት በአብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ሥፍራዎች የተሻለ እርጥበት የሚኖራቸው ሲሆን፤ ይህም ሁኔታ የበልግ የግብርና ስራን ለማከናወን፣ የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራትና ቀደም ብለው ለተዘሩና በቡቃያና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች እንዲሁም ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደለው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የሚጠበቀው እርጥበታማ ሁኔታ ለእርሻ ስራ እንቅሥቃሴ አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሮች ተገቢ የሆኑ ግብዓቶችን በመጠቀም የእርሻ ሥራውን በተሟላ መልኩ ማካሄድ  እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈም  የሚጠበቀው የተጠናከረ እርጥበት ለአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.