Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የመንገድ ግንባታ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ጎሮ ድረስ ያለውን አዲስ የመንገድ ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ የግንባታ ስራውን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀመረ፡፡

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይም ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩር ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡና ከፌዴራል መንግስት የመጡ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 4 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን የእግረኛ እና የሳይክል መንገድን ጨምሮ ከ30 እስከ 60 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት እንዳለው ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የግንባታ ስራውን አሰር ኮንስትራክሽን የሚያከናውነው ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ዩኒኮን የተባለ አማካሪ ድርጅት የሚከታተለው ይሆናል ተብሏል፡፡

ይህን የመንገድ ግንባታ ለማጠናቀቅ የወሰን ማስከበር ስራውን ጨምሮ የ24 ወራት የጊዜ ገደብ የተያዘለት ቢሆንም ግማሽ የሚሆነውን የመንገዱን ክፍል በ14 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ እንደተያዘ ተነግሯል።

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ከመጨረሻ መዳረሻው ጎሮ ሰፈራ አደባባይ በተጨማሪ ከቦሌ ሆምስ ተነስቶ በጉምሩክ በኩል አድርጎ ገርጂ ሮባ ዳቦ ጋር ያለውን ነባር መንገድ የሚያስተሳስርም ይሆናል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ጎሮ ለመሄድ በገርጂ እና ኤምፔሪያል በኩል የሚደረገውን ረጅም ጉዞ ከማስቀረቱም በላይ በአካባቢው ላይ ይፈጠር የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለማቃለል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.