Fana: At a Speed of Life!

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተደረገ ያለው ውይይት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተደረገ ያለው ውይይት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሚካሄደው ውይይት የእስካሁኑ ጉዞ እና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ዛሬ ምክክር ተካሂዷል።

ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ሐምሌ 22 2012 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ የፖለቲካ ውይይት በቀጣይነት እንዲደረግ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

በዚሁ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ባለፉት ሳምንታት ተከታታይ የውይይት መድረኮች ማካሄዱን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተካሄዱትን ውይይቶች በጋራ ለመገምገም ዛሬ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸው በጋራ መግባባት ላይ በተመሠረተ ሁኔታ ቀጣይ መንገዶችን ለማበጀትም የታለመ ነው።

በውይይቱ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የተካሄዱት መድረኮች ውጤታማ እንደ ነበሩ በመግለጽ፣ ብሔራዊ ምክክር እና ውይይትን እንዲካሄድ መንገድ ጠራጊ እንደሆኑ አመላክተዋል።

መድረኮቹ ከተካሄዱበት ዓላማ ባሻገር፣ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችም ተነስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ የፖለቲካ ውይይት መድረኮቹን ዓላማ በሚገባ የመረዳትን አስፈላጊነት አንስተዋል።

መድረኮቹ ወደ ጋራ መግባባት ለመድረስ እና የሀገሪቱን የፖለቲካ ትርክት ለማበጀት የተዘጋጁ መሆኑን አንስተው፤ መሰል ውይይቶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።

ውይይቱ ቀጣይ የውይይት መድረኮችን በቀጣይ ሳምንታት ለማካሄድ በመስማማት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የስራ ሃላፊነት ክፍፍል ተደርጓል።

ፓርቲዎች ተቀራርበው መወያየታቸውን ተከትሎ እየተገኙ ያሉ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም በውይይት መድረኩ ላይ ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.