Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የድርጅቱን የስነምግባር ደንብ በመጣስ እየፈፀሙት ያለውን አድሎ እንዲመረምርላት የድርጅቱን ስራ አስፈፃሚ ቦርድ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአሸባሪው ህወሓት አባልና የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም የድርጅቱን የአሰራር መርህ እና የስነምግባር ደንብ በመጣስ እየፈፀሙት ያለውን አድሎ እንዲመረምርላት የድርጅቱን ስራ አስፈፃሚ ቦርድ ጠየቀች።

ኢትዮጵያ ለድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ በላከችው ደብዳቤ እንዳለችው፥ ኢትዮጵያ ዳይሬክተሩን ለቦታው በማጨቷ ደስተኛ ብትሆንም ሌሎች ሃገራትና የድርጅቱ ሰራተኞች ድጋፋቸውን በመግለፃቸው ምስጋና ያቀረበች ቢሆንም ዳይሬክትሩ ግን የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ግዴታ እየተወጡ አይደለም ብላለች።

ዶክተር ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ መሆኑ በደብዳቤው ተገልጿል፡፡

እንዲሁም ሽብርተኛ ተብሎ በኢትዮጵያ ፓርላማ ለተፈረጀው የሽብር ቡድኑ ህወሃት አባል እና ደጋፊ መሆናቸውን ቀጥለውበታል ብሏል፡፡

የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነታቸውንም ለግል ፖለቲካ መጠቀሚያነት አውለውታልም ነው ያለው ደብዳቤው፡፡

የሽብር ቡድኑ ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ሽብር በግልፅ እንሚደግፉም በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ካወጧቸው ፅሁፎች መረዳት ይቻላል ነው ያለው ደብዳቤው ።

ዋና ዳይሬክተሩ ጥፋታቸውን ያቆማሉ ተብሎ ተስፋ ቢደረግም ከድርጊታቸው እንዳልተቆጠቡ ገልጿል።

የድርጅቱ ዳይሬክተርነትን በመጠቀምም የተመድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ በጠላትነት እንዲንቀሳቀሱም መሥራታቸውን አስረድቷል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ ጉዳይ በተመለከተ ሲያነሡም አድሎ በማድረግ የፈለጉትን ብቻ እንደሚመርጡም ነው የተመለከተው።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዓለም ጤና ድርጅት የዳይሬክተሮች ቦርድ በላከው በዚህ ደብዳቤ ግለሰቡ ለዚህ ወንጀላቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ህጋዊ ሂደት መጀመሩን አስታውቋል።

በመሆኑም ዋና ዳይሬክተሩ የሙያ ስነምግባር እና ከዓለም ጤና ድርጅት የአሰራር እና ስነምግባር መመሪያን የጣሰውን ተግባራቸውን እንዲመረምር እና የሚወስደውን እርምጃ እንዲያሳውቅ ጠይቋል ደብዳቤው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.