Fana: At a Speed of Life!

ከምርጫ ሂደት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ክርክሮችን የሚዳኙ ችሎቶች ሊደራጁ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመጭው ነሐሴ ወር በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚካሔደው ምርጫ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክርክሮች የሚስተናገዱባቸው የዳኝነት ችሎቶች እንደሚደራጁ የፌደራል ፍርድ ቤት ገለፀ።

በቅርቡ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1162/2012 ወደ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የሚችሉ የምርጫ ሂደት አከራካሪ ጉዳዮችን በዝርዝር ደንግጓል።

በዚህ አዋጅ ላይ የስነ ምግባር ጥሰት፣ የመራጮችና የእጩዎች ምዝገባ፣ የድምጽ ቆጠራና ውጤት አገላለጽን ጨምሮ ሌሎች ሊኖሩ የሚችሉ የምርጫ አካሔድ አከራካሪ ጉዳዮች በዝርዝር ተቀምጠዋል።

የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ንዋይ እንደገለጹት፥ ፍርድ ቤቶች የምርጫ ጉዳዮች የሚታዩባቸውን ችሎቶችን ለማደራጀት ከብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጋር እየተሰራ ነው።

በሚደራጁት ችሎቶች የሚታዩ ጉዳዮች መለየታቸውንም ጠቁመዋል።

ፍርድ ቤቶችን የማደራጀትና በምርጫ የሚነሱ ክርክሮችን የሚያዩ ዳኞችን የመደልደል ስራ የመራጮች ምዝገባ ከመካሔዱ አንድ ወር በፊት መፈፀም እንዳለበት በአዋጁ መደንገጉን ገልጸው፤ በዚሁ መሰረት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፥ ቀጣዩ ሃገር አቀፍ ምርጫ ሕጉ በሚያስቀምጠው አግባብ እንዲከናወን ለማድረግ ፍርድ ቤት ማከናወን ያለበትን ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ ይገኛል።

ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ደግሞ የፍርድ ቤቱን ተቋማዊ ነፃነት ባልተጋፋ መልኩ የምርጫ ችሎቶችን ለማደራጀት እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.