Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት  አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የደቡብ ፣  የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የሲዳማ  ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትንሳኤ በዓል  የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትም ህብረተሰቡ የትንሣኤ በዓል በመተሳሰብ እንዲያከብር  ጠይቀዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ምዕመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን እና ፍቅርን መማር ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሠው ልጆች ሲል ብዙ መከራ ተቀብሎ ይቅርታ እና ፍቅርን ያስተማረበት በዓል በመሆኑ ምዕመናን በዚህ ተምሳሌት መተሳሰብ እና በጎ ተግባርን ማጠናከር ይገባል ሲሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው  ÷ ትንሳኤ ለሰው ልጆች ሁሉ ከመከራ የመነሳት የተስፋ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ እኛም አሁን የገጠሙንን የውስጥና የውጭ ችግሮች ተቋቁመን ፈተናዎችን በፅናት ለመሻገር መነሳት ይኖርብናል ሲሉ   ገልጸዋል።

የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል ሲከበር በየአካባቢው በተከሰቱ ማንነት ተኮር ጥቃቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን ርዕሰ መስተዳድሩ  ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት ትንሳኤ አሁን ላይ እንደ ሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች ለማለፍ ምሳሌ ይሆነናል ብለዋል።

አሁን ላይ የገጠሙንን ፈተናዎች አልፈን የምንሻገር እንድንሆን ተስፋን የምንሰንቀበት በዓል ነውም ነው ያሉት።

ይህን በዓል ሰናከብር ግን ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን መጠበቅ ይገባናል ያሉት አቶ ሽመልስ  ÷በዚህ በዓል ላይ እንደተለመደው ሁሉ እርስ በእርስ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ማክበር ይገባል ሲሉም አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የትንሳኤ በአልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በሀገራችን እያየን ያለነው ጥላቻ እና መገፋፋት የክርስቲያኖች መለያ አይደለም ያሉ ሲሆን ይህን ታሳቢ በማድረግ በትንሣኤ በዓል ፍቅርን እና አንድነትን በመስበክ ማክበር ይገባል ብለዋል።

በዓሉን በማክበር ሂደት ውስጥ እራሳችንን ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በማያደርገን ሁኔታ ማክበር ይገባናልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

 

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.