Fana: At a Speed of Life!

በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ከመከላከልና ምላሽ ከመስጠት አኳያ ባሉ የህግ እና የአሰራር ማእቀፎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡
 
በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ገለታ ስዩም፣ የሴቶች ህፃናትና ባለ ብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ወይዘሪት ምዕራፍ ተስፋእየሱስ፣ ሌሎች የስራ ኃላፊዎችና እና የተለያዩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
 
ፆታዊ ጥቃት በተዛባ የስርዓተ ፆታ ግንዛቤና አስተሳሰብ ምክንያት የሚፈፀም ጥቃት መሆኑን ወይዘሪት ምዕራፍ አንስተው እነዚህ ጥቃቶች በአብዛኛው በሴቶችና ህፃናት ላይ እንደሚስተዋል ነው የጠቀሱት፡፡
 
ማንኛውም ሰው አካላዊ ጥቃት ሲያጋጥመው በመጀመሪያ የተቀናጀ የፍትህና እንክብካቤ ማዕከላት ወዳሉበት ጋንዲ፣ ጥሩነሽ ቤጅንግ፣ ሚኒሊክና ጳውሎስ ሆስፒታሎች በመሄድ ህክምናና የስነ ልቦና ምክር ማግኘት እንደሚገባውም አብራርተዋል፡፡
 
ከዚህ በተጨማሪም በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት አቤቱታ ወይም ክስ ማቅረብ እንደሚገባው ተገልጿል፡፡
 
እንዲሁም ከመደበኛ ስልጠና በተጨማሪ ኪነ-ጥበብን መጠቀም ለውጤታማነቱ የጎላ ሚና እንዳለው በመድረኩ የተነሳ ሲሆን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም የድርሻቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል፡፡
 
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በዋናነት የአምባሳደርነት ሚና ወስደው በዘርፉ ለሚስተዋሉ ችግሮች ድምፅ በመሆን እንዲያስተጋቡ ጥሪ መቅረቡን ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.