Fana: At a Speed of Life!

‹ኢትዮጵያ ስትፈራርስ ከማየት በላይ ውርደት ባለመኖሩ ትግል ላይ መሰዋት የተሻለ አማራጭ ነው›› –ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ)ኢትዮጵያ ስትፈራርስ ከማየት በላይ ውርደት ባለመኖሩ መሞት ካለብን አሸባሪው ሕወሓትን ለማስቆም በሚደረግ ትግል ላይ መሰዋት የተሻለው አማራጭ መሆኑን የኢዜማ መሪና የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ስትፈራርስ ከማየት በላይ ውርደት የለም። ያንን ውርደት ላለማየት አሸባሪው ሕወሓትን ለማስቆም በሚደረግ ትግል ላይ መሰዋት የተሻለው አማራጭ ነው ብለዋል።

‹‹እኔ ኢትዮጵያን በሚመለከት ሕወሓት ካቃተን በመሳሪያ መታገል አለብን ያልኩት ዛሬ ሳይሆን ቀደም ብዬ ነው›› ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ትግሉ በግንባር ብቻ የሚሠራ አይደለም፣ በግንባር ከሚደረገው ጦርነት ባልተናነሰ ትግሉን ለመደገፍ ሌሎች ሥራዎች አሉ ብለዋል።

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የውስጥ ደህንነታችንን ማስጠበቅ በሚኒስቴር ደረጃ ያለ ነው፡፡ እንቅስቃሴውን ለማስቆም የሚደረገውን ትግል መቀላቀል አለባችሁ ስንባል በደስታ ነው የምዘምተው።

ይሄንን ለማለት ያህል አይደለም፤ ለመዝመት በየትኛው ጊዜ ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

አሁን ሕወሓት የደቀነው አደጋ የአገር መኖር አለመኖር፣ የአንተ መኖር አለመኖር፣ የቤተሰብህ መኖር አለመኖር፣ የታሪክህ መኖር አለመኖር ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው።

በዚህ ጊዜ ጨርቄን ማቄን የሚባልበት ነገር የለም። ጊዜያዊ የፖለቲካ ስሌት ውስጥ ተገብቶም አይታሰብም ብለዋል።

መምራት ከፊት ሆኖ ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከፊት ሆኜ መምራት አለብኝ ማለታቸው ትክክል ነው። ትግሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እዝ ስር ከገባ ችግሩን ያቀለዋል በሚል ውሳኔውን ኢዜማም ይደግፈዋል።

በድርጅት ደረጃም ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

ኢዜማ የነበሩ አባሎች፣ አመራሮችና ደጋፊዎች ትግሉን በመቀላቀል በርካታ አባሎቻችን ተሰውተዋል፤አሁን ለመግባት ፍላጎት ያላቸው ስለነበሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ግልጽ አቋም መወሰዱ በበጎነት እንደሚታይ አመልክተዋል።

ሕወሓት ኢትዮጵያን ካልገዛኋት ትፈራርስ ብሎ የሚያስብ ሃይል መሆኑን በመጠቆምም፤ አቅሙን በመጠቀም በሌሎች ክልሎች ያሉ አክራሪ ብሄርተኞችን በመጠቀም አገር ለማፍረስ እንደሚሰራ፣ ያንን ካላደረገ አርፎ እንደማይቀመጥ ቀደም ሲል መናገራቸውንና ዛሬ ሲከሰት ብዙ አለመገረማቸውን አስታውሰዋል።

ይሄንን ሃይል መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት በመክፈል ማስቆም ካልተቻለ ጥያቄው መንግሥት ይወድቃል አይወድቅም ሳይሆን አገር ይኖራል አይኖርም የሚል ነው።

አሸባሪው ሕወሓት ካልተደመሰሰ ኢትዮጵያ ትኖራለች ብዬ ከልቤ አላምንም ሲሉም ነው የገለጹት።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.