Fana: At a Speed of Life!

የበይነ መረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን ለማሻሸል ከኢንተርኔት ካፌዎች ጋር ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የበይነ መረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ተደራሽነት፣ ፍጥነትና የተገልጋዩን የግልጋሎት ቅልጥፍና ለማሻሻል በኢንተርኔት ካፌ የንግድ ስራ መደብ ተሰማርተው ከሚሰሩ የንግድ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጅት ማድረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ በማድረግ ደንበኞች በማንኛውም ቦታ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ አማራጮችን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተሩ ፀጋው በለጠ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ የተጠቃሚዎችን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብና እንግልትን በማስቀረት ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፥ እንደ ሀገር ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ በንግድ ስራ ከተሰማሩ የዘርፉ ተገልጋዮች ውስጥ ከ1 በመቶ የማይበልጡት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለተጠቃሚዎች የተሻለ አማራጭና የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ለንግዱ ማህበረሰብ ጊዜንና ገንዘብን ቆጣቢና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉ አማካሪ ግዛው ተክሌ በበኩላቸው፥ የበየነመረብ ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቱን ሁሉን አቀፍና ተደራሽ ለማድረግ ከኢንተርኔት ካፌ ባለቤቶች ጋር አብሮ መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ስርዓቱ የሚመራበት ህጋዊና ተቀባይነት ያለው የስራ ውል የሚያስፈልግ በመሆኑ፥ የተዘጋጀው የውል ሰነድ በህግ ባለሙያዎች አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ የኢንተርኔት ካፌ ባለቤቶች የበየነመረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር በመፈራረም ወደ ስራ ይገባል ተብሏል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.