Fana: At a Speed of Life!

የዘንድሮው የሸዋል ኢድ በዓል ከዳያስፖራዎች ጋር የምናከብረው በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮው የሸዋል ኢድ በዓል ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪን ተቀብለው ከመጡ ዳያስፖራዎች ጋር የምናከብረው በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡

በሐረሪ ክልል የኢድ -አል ፈጥር በአል በተከበረ በሣምንቱ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው የሸዋል ኢድ በዓል የሐረርን ታሪክ፣ እሴትና ባህልን ሊያስተዋውቁና ሊገልጹ የሚችሉ ዝግጅቶችን በወንድማማችነት መንፈስ ለታዳሚው ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሸዋል ኢድ በአልን ለማክበርና ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ያለምንም የፀጥታ ችግር በአግባቡ ለማስተናገድና በዓሉን ለማክበር ጭምር ዝግጅት መደረጉንም ነው የተናገሩት፡፡

በዛሬው ዕለትም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ የካቢኔ አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በክልሉ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች የ” ሸዋል ኢድ” በዓልን ምክንያት በማድረግ ተመርቀዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የገጠር ጥርጊያ መንገድና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡

በሐረሪ ክልል የሸዋል ኢድ በዓል ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት 2 በድምቀት ይከበራል።

በአዲሱ ሙሉነህ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.