ኢትዮጵያና ጣልያን የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በትብብር ለመከላከል ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ጣልያን ለፖሊስ ተቋማት የጋራ ስጋት የሆኑ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በትብብር ለመከላከል ተስማሙ፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የጣልያን የካራቢኔሪ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ከሆኑት ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቸውም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጥበቃን የሚያግዙ የፖሊስ ፓትሮል ጀልባዎችን በድጋፍ ለመስጠትና ሙያዊ እገዛ ለማድረግ እንዲሁም በፖሊስ አመራር፣ በፎሬንሲክ ሳይንስ እና በልዩ ጥበቃ (ቪአይፒ) ስልጠና በመስጠት አቅም ለመገንባት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ እየተገነባ ላለው የፎሬንሲክ ሳይንስ ኢንስቲትዩት የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የጋራ ስጋት የሆኑ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በትብብር ለመከላከል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡