Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል በ2015 በጀት አመት ከ25 ሚሊየን ኩንታል ምርት በላይ ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የክልሉን የምግብ ዋስትናና ምርታማነት ለማረጋገጥ ብሎም በግብርናው ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑንም የሶማሌ ክልል መንግሥት አስታውቋል፡፡

በክልሉ የሚከሰተው ድርቅ መፍትሄ ለመስጠት፣ ከእርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅና የክልሉን ህዝብ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በክልሉ ያለውን ለም መሬት፣ የከርሰ ምድርና የዝናብ ውሃ ሃብት ጥቅም ላይ በማዋል የተቀናጀ የግብርና ስራ ለመስራት እቅድ ተነድፎ ወደ ስራ ተገብቷል ነው የተባለው።

የግብርና ምርትና ምርታማነት ሥራዎች ከዳር ለማድረስና የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እንዲሁም እንደሀገር የታቀደውን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በ153 ሚሊየን ብር ወጪ የክልሉ መንግሥት 160 ዘመናዊ ለግብርና ሜካናይዘሽን የሚሆኑ ትራክተሮች ግዢ በመፈፀም ለግብርና ስራው ዝግጁ ተደርገዋል።

እንደ ክልል ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶችንና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በመጠቀም ከባህላዊ የግብርና ዘዴ በመላቀቅ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት በ2015 በጀት አመት ከ25 ሚሊየን ኩንታል ምርት በላይ ለመሰብሰብ እቅድ ይዟል።

በሌላ በኩል ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችና የኮንትሮባንድ ንግድን በመከላከልና አለ አግባብ በሸቀጦች ላይ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ድጋፍ በማድረግ የዋጋ ግሽበትን መንግሥት ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ደግሞ የክልሉ የፀጥታ ተቋማት በተቀናጀ መልኩ እየሰሩ ነው የተባለ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር በሶማሌ ክልል በኩል የምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች የክልሉ ልዩ ሀይል ሰራዊት ሌተቀን እየጠበቀ ሲሆን፥ ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት የሞከሩ ፀረ ሰላም ሀይሎችን በተደጋጋሚ አክሽፏል ነው የተባለው።

በክልሉ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ፣ በክልሉ ባጋጠመው የድርቅ አደጋና በሀገርና በአለም ላይ የተከሰተው የኢኮኖሚ ጫና አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በማሳደሩ፣ በበጀት አመቱ ያልተጠናቀቁ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግስት አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከክልሉ ገቢ ጋር በተያያዘ፣ ባለፉት 10 ወራት 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፥ በዚህም የእቅዱ 88 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

ከፍትህ ተቋማት ጋር በተያያዘ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኙ የፍትህ አካላትና ዳኞች ስልጠናና የአቅም ግንባታ ትምህርቶች የተሰጣቸው መሆኑ ተገልፆ የክልሉን የፍትህ ሥርዓት እንዲሻሻል ተደርጓል፤ ይህም ዜጎች በፍርድ ቤቶች ላይ ያላቸው እምነት ከፍ ብሏል ነው የተባለው።

የክልሉ የፍርድ ሥርዓት ቀልጣፋና ፍትህ የሰፈነበት ይሆን ዘንድ በፍርድ ቤቶችና በዳኞች ላይ ጥልቅ ሪፎርም የተደረገ ሲሆን÷ በስነምግባር ጉድለት፣ በአቅም ማነስ፣ በስራ ገበታ ላይ ባልተገኙ 27 ዳኞች ከስራ እንደታገዱ ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአጠቃላይ የሶማሌ ክልል በ2015 የበጀት አመት ለግብርና ልማት፣ ለውሃ ልማት፣ ለመስኖ ስራና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ትልቅ ትኩረት በመስጠት ወደ ስራ መግባቱን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.