Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ በቀዳሚነት የተወያየው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡
የሀገሪቱን ወቅታዊና ዘላቂ የግብርና ልማት ፍላጎት በውጤታማ ምርምር ለማሳለጥ የሚያግዙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማልማት፣ የግብርና ምርምር ሥርዓቱን በማስተባበር፣ በመደገፍና በማበረታታት እንዲሁም ተቋማዊ ትስስርን በማጎልበት በግብርና ምርቶች ራስን ለመቻል ብሎም የወጪ ንግድ ግብን ለማሳካት ግልጽ ተልዕኮና ኃላፊነት ያለው ተቋም ማቋቋም በማስፈለጉ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ወቅቱ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት ጋር የሚራመድ፤ የዜጎችን እና የአካባቢን ደህንነትና ጤንነት ያረጋገጠ እንዲሆን እንዲሁም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች በተገቢው ወጪ፣ ጊዜ እና ጥራት መፈፀማቸውን በመቆጣጠር እና በመደገፍ የኢንዱስትሪውን ብቃትና ተወዳዳሪነት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የባለስልጣኑን አደረጃጀት እንዲሁም ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮበሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተወያየው የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደርን እና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደርን ለማቋቋም በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ነው፡፡
የተቋማቱን አሠራር እና የመፈፀም አቅም ማላቅ፤ አደረጃጀቶቻቸውን ማዘመን እና ስልጣንና ተግባሮቻቸውን ግልፅ ማድረግ በማስፈለጉ፣ በተለይም ተቋማቱ የሚሰበስቡትን የጡረታ ፈንድ ትርፋማና አዋጭ መሆናቸው በጥናት በተለዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በማዋል ሀገራቸውን አገልግለው ጡረታ ለሚወጡ ዜጎች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ቀጣይነት እና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ነባሮቹን ደንቦች ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.