የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የ18 ቢሊየን ዶላር ብድር ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የ18 ቢሊየን ዶላር የረጅም ጊዜ ብድር ለመስጠት ማቀዱን አስታውቋል፡፡
የህብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ቫልዲስ ዶምብሮቭስኪስ እንደገለፁት÷ የአውሮፓህብረት ለዩክሬን ለመስጠት ያቀደው ብድር በ35 ዓመታት ውስጥ የሚመለስ ነው፡፡
ህብረቱ ገንዘቡን ከዓለም አቀፍ ገበያ በመበደር ለዩክሬን የሚሰጥ ሲሆን÷ የብድሩ ወለድም በህብረቱ የሚሸፈን መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ ኪዬቭ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋታል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ÷ የህብረቱ ሀገራት ብድሩን በዓመቱ መጨረሻ ላይ እንዲያጸድቁት ጠይቀዋል፡፡
ብድሩን ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉም የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ይሁንታ የሚያስፈልግ ሲሆን÷ ሀንጋሪ በገንዘብ ብድሩ ላይ አለመፈረሟ ተመላክቷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን ቃል ከገባው 9 ቢሊየን ዶላር ብድር ውስጥ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላሩን የሰጠ ሲሆን÷ 2 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ለኪዬቭ ወታደራዊ ድጋፍ መዋሉን አር ቲ ዘግቧል፡፡