Fana: At a Speed of Life!

በትንሣኤው ብርሃን ሁላችንም ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሰላም መሣሪያዎች እንሁን – ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁላችንም በትንሣኤው ብርሃን ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሰላም መሣሪያዎች እንሁን ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ገለጹ፡፡

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ፥ ለክርስቲያኖች ትልቁ ምስጢራችን የትንሣኤ የምሥራች ነው ፤ የሰው ልጅ ሕይወት በሞት የሚደመደም እንዳልሆነ የክርስቶስ መነሣት ያስተምረናል ብለዋል፡፡

እነሆ የዓለም ንጉሥ ተነሥቷልና እንቀበለው፤ እናክብረው፤ እናመስግነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሁላችንም በትንሣኤው ብርሃን ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሰላም መሣሪያዎች እንሁን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የችግሮቻችን መውጫ ቁልፍ ሰላም ብቻ ነው ያሉት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ፥ ለሰላም እንጸልይ እንትጋ ፤ ሰላምንና ፍቅርን ጌታ በትንሳኤው ያድለን ብለዋል፡፡

ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን፣ የተሰደዱትን፣ የተፈናቀሉትንና የተራቡትን፣ በግጭቶች ዙሪያ የሚገኙትን በማሰብና በመርዳት መሆኑን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በትንሣኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለታመሙት ምሕረትን፤ ላዘኑት መጽናናትን፤ በየማረሚያ ቤቶች ለሚገኙት መፈታትን፤ በችግርና በመከራ ላይ ለሚገኙት ብርታትን ለሀገራችንና ለህዝባችን ሰላምን ይስጥልን ሲሉም ተመኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.