Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትወርክ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትወርክ የመጀመሪያ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

ቴሌሜዲሲን ኔትዎርኩ ኢትዮጵያ ውስጥ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር በመተባበር የጀመሩት መሆኑ ታውቋል፡፡

በመርሐ ግብሩም ሀባሪዶክ የተሰኘ ታካሚዎች ባሉበት ሆነው የሚፈልጉትን ማንኛውም የጤና ባለሙያ በማነጋገር ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚረዳ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይፋ ተደርጓል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ቴሌሜዲስን ለመድረስ አስቸጋሪ ለሆኑ ቦታዎች በቀላሉ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እና ጥራት ለማሻሻል ተመራጭ ዘዴ ነው ብለዋል።

ዲጂታል ጤና ወጪን ከመቀነስ ባሻገር የአገልግሎት ጥራትን በመጨመር እና የተገልጋይ እርካታን በማሳደግ እንዲሁም በባለሙያዎች መካከል የእውቀት ሽግግር በማሳለጥ ውጤታማነትን የሚያሻሽል እንደ ሆነም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፈተናን ለመቋቋም በ2020 የተወሰኑ የጤና አገልግሎቶችን ለመስጠት የቴሌሜዲሲን አሰራርን ተግባራዊ ማድረጉን እና ውጤታማነቱም አበረታች እንደሆነም አስረድተዋል።

አሁን የተጀመረው የአፍሪካ ቴሌሜዲሲን ኔትዎርክም የጤና አገልግሎትን ለማዘመን እና የህብረተሰቡን እንግልት እንዲሁም ወጪውን በመቀነስ ረገድ የተጀመሩ የቴሌሜዲሲን ስራዎችን ከማቀናጀት አንጻር አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

የአፍሪካ ቴሌሜዲሲን ኔትዎርክ መስራች ዶክተር አከዛ ጠዓመ በበኩላቸው በዘመናዊ ተክኖሎጂ የታገዘ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ የአፍሪካን የጤና ስርዓት ከማገዙም በተጨማሪ በርካታ የጤና ባለሙያዎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ እንደሚረዳ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.