Fana: At a Speed of Life!

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና የግል ከፍተኛ ተቋማት ምሁራን የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም የግል ከፍተኛ ተቋማት ምሁራን የውይይት መድረኮች በአዲስ አበባ እየተካሄዱ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም “የሀገረ-መንግሥት ግንባታና የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የምርምር ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላትን ያካተተ ሀገራዊ የምሁራን የምክክር መድረክ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር መካሄዱ ይታወሳል፡፡

በዛሬው ዕለት እየተካሄዱ ያሉ መድረኮችም የዚሁ ውይይት አካል መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምሁራን ውይይት እያደረጉ ነው፡፡

የውይይት መድረኮቹ ዓላማም በተለያዩ መስኮች ያሉ ምሁራንና ሊሂቃን በሀገር ጉዳይ በጋራ በመወያየት ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማገዝ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማስቻል መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምሁራን ምርምር ተኮር መፍትሄዎችን በማመላከት ለኀገር ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻልም የምሁራን መድረኩ ዓላማ እንደሆነ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ያላቸውን ሚና በሚገባ ተገንዝበውና አቅማቸውን አሰባስበው ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በሚጠበቅባቸው ልክ እንዲሰሩ ማስቻልም ከውይይቱ ዓላማዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.