Fana: At a Speed of Life!

በ433 ሚሊየን ብር ወጪ የተንዳሆ የመስኖ አውታር ግንባታና የጎርፍ መከላከል ዳይክ ጥገና እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ በ433 ሚሊየን ብር ወጪ የተንዳሆ ፒ.ሲ. 16 የመስኖ አውታር ግንባታና የጎርፍ መከላከል ዳይክ ጥገና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 46 ነጥብ 35 በመቶ መድረሱም ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ጎርፍ በመከላከልና ጉዳት የደረሰበትን 2 ሺህ 521 ሄክታር የመስኖ አውታር በመገንባት ለአርብቶአደሩና ለፊል አርብቶአደሩ አገልግሎት ላይ ማዋል መሆኑ ታውቋል፡፡

በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ዋና ዋና ስራዎችም የኮንትራክተር መሰረተ ልማት ግንባታና ጥገና ፣ የቦይ ምንጣሮ ስራዎች ፣ የሶስት ኩሬዎች ስራ፣ የመስኖ ቦይ ፣የዳይክ ጥገና ፣ የመስኖ አውታር ጥገና እና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጠረጋ ስራዎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ፕሮጀክቱ የተጀመረው በ2013 ዓ.ም ህዳር ወር ላይ ሲሆን÷ የዲዛይን ክለሳ በማድረግ በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም የጥገናና ግንባታ ስራው ዳግም መጀመሩን ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.