Fana: At a Speed of Life!

የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ተማሪዎች ድጋፍ እንዲደረግ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ቡድን ምክንያት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከቀያቸውና ከትምህርት ገበታቸው ለተፈናቀሉ ተማሪዎች ሁሉም ወገን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ የአማራ፣ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጥሪ አቀረቡ፡፡
 
የአማራ፣ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች “ ስለኢትዮጵያ” ከተሰኘው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር ዛሬ ቆይታ አድርገዋል።
 
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማተቤ ማንደፍሮ እንዳሉት፥ የመምህራን ኮሌጆችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ጨምሮ 4 ሺህ 107 ትምህርት ቤቶች በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ወድመዋል፡፡
 
በዚህም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸውን ጠቅሰው፥ 11 ሺህ 600 መምህራን ደግሞ ስራ ማቆማቸውን ተናግረዋል፡፡
 
ተጨማሪ ምርመራዎች የሚያስፈልጉ ቢሆንም ትምህርት ቤቶቹ ላይ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲሰላ ከ11 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚሆን ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡
 
ከትምህርት ገበታቸው የተስተጓጎሉ ተማሪዎች የአገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፋንታ የሚወስኑ በመሆናቸው መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 
ተማሪዎቹ የደረሰባቸውን የሥነ ልቡና ጉዳት ለመቀነስም የሚመለከታቸው አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በበኩላቸው፥ ለአንድ አገር እድገት ትልቁ መሰረት ትምህርት መሆኑን ገልፀው፥ በአሸባሪው ህወሓት የተፈናቀሉ የአፋርና አማራ ክልል ተማሪዎችን ለማቋቋም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
 
የአሸባሪው ህወሓት የቀድሞ የአገዛዝ ዘመን እንዲያበቃ የተማሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር የገለፁት ኃላፊው፥ አሁን ላይም ተማሪዎች የዘማች ቤተሰብ ሰብሎችን በመሰብሰብ ድጋፋቸውን በተግባር እያሳዩ መሆናቸውን በመጥቀስ አድንቀዋል።
 
አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ተማሪዎች ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ፣ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ በብሄራቸው ላይብቻ እንዲያተኩሩ አድርጓል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ናቸው፡፡
 
በመዲናዋ ያሉ ተማሪዎች የአሸባሪውን የህወሓት ወረራና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ ከማድረግ በተጨማሪ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ አጋርነታቸውን አሳይተዋል ብለዋል፡፡
 
አገሪቱን ያጋጠሟት ችግሮች በአብዛኛው ያለፈው የትምህርት ስርዓት ውጤት መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘላለም፥ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ተማሪዎችን በአዳዲስ የትምህርት ስርዓቶችና ፕሮግራሞች መገንባት ይገባል ነው ያሉት።
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.