Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት ወደ ትግራይ ላለመግባት ያሳለፈው ውሳኔ ችግሩን ከጦርነት ውጭ ለመፍታት ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት ሜዳ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ወደ ትግራይ አልገባም ብሎ ያሳለፈው ውሳኔ ችግሩን ከጦርነት ውጭ ለመፍታት ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት ሜዳ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ የሚፈፀመውን ወታደራዊ ዕርምጃ ላለመቀጠል መወሰኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ውሳኔው ከጦርነት ውጪ ያሉ ሌሎች የመፍትሄ አማራጮችን ለማጤን ዕድል የሚከፍት በመሆኑ÷ ብዙዎች በደስታ ተቀብለውታል፤ አሁን ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት አደባባይ ነው ሲሉም ሁኔታውን አስረድተዋል።
አሜሪካ ግን ከዚህ የኢትዮጵያ አካሄድ በተቃራኒው መቆሟን የገለጹት አቶ ደመቀ÷ ኢትዮጵያ ለሚደርስባት ግፊት አልንበረከክም በማለቷ የአሜሪካን አስተዳደር የሚያደርስባት ጫና መበርታቱንም አስረድተዋል፡፡ በዚህም የአሜሪካ መንግሥት አንዳንድ የችኮላ ውሳኔዎችን ወስኗል፡፡ በዚህም እናዝናለን ብለዋል።
የአሜሪካ አስተዳደርና የህግ አውጭ አካላት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ላይ በሚጥሏቸው ማዕቀቦችንና ዕርምጃዎች ከፍተኛ ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን በቃህ ካሉት ቆይተዋል ያሉት አቶ ደመቀ÷ የዓለም ማኀበረሰብ ይህንን በአግባቡ ቢረዳ ኖሮ ይህ ሁሉ ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻዎች በኢትዮጵያ ላይ አይፈጠሩም ነበር ብለዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወቅታዊው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያለውን አቋም እንደገና እንዲያድስና እንዲመለከት ጥብቅ በሆኑና በማያሻማ መልኩ ኢተዮጵያ ታሳስባለች ብለዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን የፈረንጆቹን 2022 አዲስ ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው የህልውናና የህብረ-ብሔራዊ አንድነት ዘመቻ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ከመቼውም ጊዜ ከፍ ባለ ሁኔታ እንዳጠናከረው አንስተዋል።
ከአገር ውስጥ ባለፈ ኢትዮጵያ ከተለያየ አቅጣጫዎች ድጋፍ ነበራት ያሉት አቶ ደመቀ÷ ጫናዎች በበዙበት ወቅት ኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጆችንም አግኝታለች። ኢትዮጵያም ለእነዚህ የአፍሪካና በሌሎች ክፍላተ ዓለም ለሚገኙ ወዳጅ አገራት ለህልውናችን ለምናደርገውን ትግል ለሰጡት የማያቋርጥ ድጋፍ ታመሰግናለች ብለዋል።
በተጨማሪ ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የተውጣጡ ሰዎች ኢትዮጵያን ለመደገፍ ዓለም አቀፉን የ #Nomore እንቅስቃሴን ሲቀላቀሉ ማየትም ልብን የሚያሞቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አሁን ያለው ትውልድ በቀደምት አባቶቹና በአያቶቹ የጀግንነት ታሪክ የሚኮራበትን ያህል፣ ሌሎች ሊያስብባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም አሉበት ያሉት አቶ ደመቀ÷በተለይም ሃሳብን መግለጽና ለመግባባት የሚረዱ የማያቋርጡ ውይይቶች የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ መንግሥት ሁኔታዎችን በተቻለ ፍጥነት የማመቻቸትና የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበትም ገልጸዋል። ለአገራዊ ምክክሩ የሚረዳ አስፈላጊው መሠረት ተቀምጦ ምክክሩ በቅርቡ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ዋና ዋና ልዩነቶቻችችን ለመፍታት የሚረዳው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ውይይት ኮሚሽንም ማቋቋሚያ አዋጅ ፀድቋል።
የኮሚሽኑ አላማ በጋራ ታሪካችን ላይ የጋራ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ፣ አሁን ላለንበትና በትውልዶች መካከል ላሉት ተግዳሮቶች የጋራ መፍትሄዎችን ለመፈለግ እንዲሁም የቀጣይ መንገዳችንን ለመቅረጽ የሚረዳ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አሁን የተፈናቀሉ ዜጎቿን መልሶ የማቋቋም፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባትና የማደስ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እያደረገች ነው። በዚህም ለዜጎች አገልግሎቶች መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመልዕክታቸው ማስተላለፋቸውን ከውጭ ጉይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.