Fana: At a Speed of Life!

የኮሌራ በሽታን ማጥፋትና መቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ እቅድ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮሌራ በሽታን ለማጥፋትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ገለጸ።

የኢንስቲቲዩቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የባክቴሪያ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ቡድን ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።

በአውደ ጥናቱ የትምህርት፣ የግብርና፣ የጤና፣ የውሃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የአደጋ መከላከል ኮሚሸን፣ የሁሉም ክልል የውሃና የጤና ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና የተለያዩ አጋር ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

አውደ ጥናቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ መስሪያ ቤቶችና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባባር ኮሌራን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማጥፋትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ ሰነድ ለማዘጋጀት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የሚዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ በ2030 በሀገር አቀፍ ደረጃ ኮሌራን ለማጥፋት እና በበሽታው የሚሞቱትን ቁጥር በ90 በመቶ ለመቀነስ የተያዘውን ፕሮግራም በተሻለ ደረጃ ጥንካሬ የሚሰጥ መሆኑ ተመላክቷል።

በኢንስቲቲዩቱ የባክቴሪያ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ሰጪ ቡድን ሃላፊና የአውደ ጥናቱ አስተባባሪ አቶ ሙከሚል ሁሴን፥ ኮሌራን ለማጥፋት ከሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የኮሌራ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን የመለየት እና ሌሎችም በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

የኮሌራ ማጥፊያና መቆጣጠሪያ ረቂቅ ሰነዱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር ዓለም አቀፍ የኮሌራ ማጥፊያና መቆጣጠሪያ ግብረ ኃይል ያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ መሰረት አድርጎ የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ረቂቅ ሰነዱ ከተዘጋጀ በኃላ በድጋሚ በባለድርሻ አካላትና በከፍተኛ ሃላፊዎች ተገምግሞ ለዓለም አቀፍ የኮሌራ ማጥፊያና መቆጣጠሪያ ግብረ ኃይል እንደሚቀርብም አስረድተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋዎች እና ምላሽ አስተባባሪ ዶክተር አግሪ ቢተግሪንዝ በረቂቅ ሰነዱ አጠቃላይ ሁኔታ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከኢንስቲቲዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.