Fana: At a Speed of Life!

የገቢዎች ሚኒስቴር ግብር ከፋዮችን አመሰገነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በግማሽ ዓመቱ ለተመዘገበው የላቀ የገቢ አፈፃፀም ግብር ከፋዮችን አመሰገነ።

የምስጋና መርሃ ግብሩ በትናንትናው እለት ምሽት መካሄዱን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፥ ሚኒስቴሩ በ2012 ዓ.ም በግማሽ ዓመቱ 125 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 102 በመቶ ማሳካቱን ገልፀዋል።

ይህ እቅድ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 29 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ብልጫ አለው ብለዋል።

ከዓመቱ እቅድም 52 በመቶ የተሳካ ሲሆን፥ ግብር ከፋዮች በወቅቱና በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈላቸው ለዕቅዱ መሳካት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ከምን ጊዜውም በላይ 85 በመቶ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በፈቃደኝነትና በወቅቱ የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈላቸውም ለገቢ እድገቱ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም አንስተዋል።

በቀጣይ ግማሽ ዓመትም በስኬታማ ጉዞው እንቀጥላለን ያሉት ሚኒስትሯ፥ ግብር ከፋዮች እስካሁን ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ግብር ከፋዮች በበኩላቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ይህንን የምስጋና መርሃ ግብር በማዘጋጀቱ አመስግነው፥ ግብርን በፈቃደኝነትና በታማኝነት በመክፈል በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ልማት ለመደገፍ ወደፊትም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ከሚያተርፉት ትርፍ ግብር መክፈል የውዴታ ግዴታ ቢሆንም በሚከፍሉት ግብር ሀገር ስትለማ ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው፥ በቀጣይም ከሚኒስቴሩ ጎን በመቆም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.