ኢትዮጵያ በ2021 የምታስተናግደው ጉባኤ ላይ ከመላዉ አለም የተውጣጡ የአይ. ሲ.ቲ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ ተባለ
አዲስ አበባ፣የካቲት 14፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)ኢትዮጵያ በ2021 የምታስተናግደው አለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን ጉባኤ ላይ ከመላዉ አለም የተውጣጡ ወጣት የአይ. ሲ.ቲ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ ተባለ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሀም በላይ ከአለምአቀፍ ቴሌኮም ልማት የአፍሪካ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ሚስተር አንድሪው ሩጄጄ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይታቸውም ትኩረቱን ያደረገው በ2021 በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የአለምአቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን ልማት ጉባኤ (WTDC-21)የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ላይ ነው ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ጄኔቫ ከሚገኘው አለምአቀፍ ቴሌኮምኒኬሽን ልማት ጽህፈት ቤት እና ከአፍሪካው ጽህፈት ቤት ጋር በመነጋገር በርካታ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኗም በውይይታቸው መነሣቱ ተገልጿል፡፡
በጉባኤው ላይ ከ193 ሀገራት የተውጣጡ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከዛ ዉስጥ 90 ሚኒስትሮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተገለጸው፡፡
የዘንድሮውን ጉባኤ ከመላው አለም የተውጣጡ ወጣት የዘርፉ ባለሙያዎች መድረክ በማዘጋጀትና የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች ለማስፈጸም አዳዲስ አሰራሮችን በመፍጠር ለየት ይላልም ተብሏል፡፡
አይ.ሲ.ቲ ለስራ ፈጠራና ሀገር ልማት እንዲሁም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ የወጣቱን ሚና ለማጉላት ለሁለት ቀናት በሚካሄድው መድረክ ላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የዘርፉ ወጣት ባለሙያዎችም ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ ከጥር 24 እስከ 27 በሚካሄደው የአለም አቀፎ ቴሌኮምኒኬሽን አማካሪ ቡድን መድረክ ላይ ተሳትፋ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዙርያ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቀርብም መጋበዟም ነው የተገለጸው።
በ2019 የተካሄደው አለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ጉባኤው ላይ በ2021 የሚካሄደውን የአለምአቀፍ ቴሌኮም ልማት ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ በሙሉ ድምፅ መምረጧን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡