Fana: At a Speed of Life!

ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እጅግ አሰቃቂና ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብአዊነት ያፈነገጠ ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ መንግስት ገለፀ።
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ድርጊት መፈጸሙን አንስቷል።
 
በማህበራዊ ትስስር ገፆች በተንቀሳቃሽ ምስል ሲዘዋወር በቆየው እጅግ አሰቃቂ ድርጊት ንፁሃን ዜጎች በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ሲደረግ መታየቱ በመግለጫው ተመላክቷል።
 
ይህ ድርጊት ከኢትዮጵያዊነት ባህል፣ እሴትና ከማንኛውም የሰብዓዊነት እሳቤ ያፈነገጠና እጅግ አሰቃቂ ወንጀል ነው ያለው አገልግሎቱ፥ ይህ እኩይ ድርጊት መጠፋፋትን ያፈጥን ካልሆነ በቀር ሰላምንም ሆነ ፍትህን እውን ሊያደርግ እንደማይችልም አስገንዝቧል።
 
በመሆኑም ድርጊቱ ሊኮነንና ሊወገዝ ይገባል፤መነሻቸውም ሆነ ማንነታቸው ምንም ይሁን ምን መንግስት ይህን አይነት ፍፁም ከሰብዓዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
 
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ህገወጥነት ለመቆጣጠርና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከልም ከክልሉና ከመላው የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
 
የንፁሃን ዜጎችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን መንግስት ከዚህ በኋላ አይታገስም ያለው መግለጫው÷እነዚህ በወንጀል ስራ ላይ የተሰማሩና የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም በጥብቅ አሳስቧል።

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.